ኢንጂነር አይሻ መሀመድ በአፍሪካ የመጀመሪያዋ ሴት የመከላከያ ሚኒስትር እንደሆኑ በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የቀረበው መረጃ የተሳሳተ ነው

መጋቢት 2፣ 2018
/ኢትዮጵያ ቼክ/- “ክብርት ኢንጂነር አይሻ መሀመድ በኢትዮጵያና በአፍሪካ ብቸኛ የመጀመሪያ ሴት መከላከያ ሚንስትር” የሚል መረጃ በማህበራዊ ትስስር ገጾች እየተጋራ ይገኛል።
ይህ መረጃ ሰሞኑን የተከበረዉን አለም አቀፍ የሴቶች ቀን በማስመልከት የተጋራ ሲሆን መረጃዉን ካጋሩት መካከልም የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የተረጋገጠ (verified) የፌስቡክ ገጽ ይገኝበታል።
በፌስቡክ ገጹ ሌሎች በሀገሪቱ በተለያዩ የስራ መስኮች ቀደምት የሆኑ ሴቶች ዝርዝርም የተጋራ ሲሆን መረጃዉን በርካታ የፌስቡክ ተጠቃሚዎች መልሰዉ አጋርተዉታል።
ይሁን እንጂ “ኢንጂነር አይሻ መሀመድ በኢትዮጵያና በአፍሪካ ብቸኛ የመጀመሪያ ሴት መከላከያ ሚንስትር” በሚል የተጋራዉ መረጃ በከፊል የተሳሳተ መሆኑን ተመልክተናል።
ኢ/ር አይሻ በኢትዮጵያ የመጀመሪያዋ ሴት መከላከያ ሚንስትር ቢሆኑም በአፍሪካ ግን የመጀመሪያዋ እንዳልሆኑ መረጃዎች ያመለክታሉ። ኢትዮጵያ ቼክ በዚህ ዙሪያ ባደረገዉ ማጣራት የተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት ከኢትዮጵያ አስቀድመዉ ሴት መከላከያ ሚኒስትሮች ነበሯቸው።
ከነዚህ መካከል ፍሎሜና ማስካሬናስ እኤአ ከ2003-2004 ጊኒ ቢሳውን የመከላከያ ሚንስትር በመሆን አገልግለዋል።
ሴሲል ማኖራሃታ ደግሞ እኤአ ከ2007-2009 የማዳጋስካር መከላከያ ሚንስትር ነበሩ።
በተጨማሪም ኤልሳ ማሪያ ኔቶ ዲ’ኣልቫ ቴሼራ ዲ ባሮስ ፒንቶ እኤአ ከ2008-2010 የሳኦ ቶሜ እና ፕሪንሲፔ መከላከያ ሚንስትር ሆነው አገልግለዋል።
ስለዚህ “ኢንጂነር አይሻ መሀመድ በኢትዮጵያና በአፍሪካ ብቸኛ የመጀመሪያ ሴት መከላከያ ሚንስትር” በሚል የተጋራዉ መረጃ አሳሳች ሆኖ አግኝተነዋል።
ኢትዮጵያ በ2011 ዓ.ም ኢንጂነር አይሻ መሀመድን ጨምሮ በርካታ ሴቶችን የሀገሪቱ 50% የሚሆን የሚንስትርነት ቦታዎች ላይ ስትመደብ አድናቆትን አግኝታ እንደነበር ይታወሳል።
ኢትዮጵያ ቼክ
ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ
ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::





