አቶ ሽመልስ አብዲሳ በአቡ ዳቢ ከተማ ህክምና ላይ እያሉ ‘ያሳያሉ’ በሚል እየተጋሩ ያሉ ምስሎች በሰው ሰራሽ አስተዉሎት (AI) የተፈበረኩ ናቸው

መጋቢት 11፣ 2018

/ኢትዮጵያ ቼክ/- ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ በገጠማቸዉ የጤና እክል ምክንያት በተባበሩት አረብ ኢሚሬቶች፣ አቡ ዳቢ ህክምና ላይ መሆናቸዉን የሚጠቁሙ መረጃዎች በስፋት እየተጋሩ ይገኛሉ።
ፕሬዝዳንቱ በሀገሪቱ በሚገኝ በአንድ የህክምና ተቋም ዉስጥ ተኝተዉ ሲታከሙ ያሳያሉ የተባሉ ምስሎችም በማህበራዊ ትስስር ገጾች በስፋት እየተጋሩ ይገኛሉ።
ኢትዮጵያ ቼክ የክልሉ ፕሬዝዳንትን አሁናዊ የጤና ሁኔታ በተመለከተ ዝርዝር መረጃ ባያገኝም በተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ህክምና ላይ እንዳሉ ስማችን አይጠቀስ ካሉ የመንግስት ምንጮች ሰምተናል።
ይሁንና እንደ ‘SynthID Detector’ እና ‘Hive Moderation’ ያሉ በሰው ሰራሽ አስተውሎት የተሰሩ ምስሎችን መመርመሪያ መሳሪያዎችን በመጠቀም እንዲሁም ትልቅ ምልከታዎችን በማድረግ እየተጋሩ ያሉ ምስሎችን መርምረናል።
በዚህም መሰረት ፕሬዝዳንቱ አቡ ዳቢ በህክምና ተቋም ዉስጥ ተኝተዉ ህክምና እየተከታተሉ እንደሆነ ያሳያሉ በሚል እየተጋሩ ያሉ ምስሎች ትክክለኛ እንዳልሆኑ አረጋግጧል።
ለምሳሌ ያክል ‘Daily Facts’ እና ‘Daandii Dhugaa’ በተሰኙ የፌስቡክ ገጾች የተጋሩ ምስሎች በጉግል ኤ አይ (Google AI) የተፈበረኩ እንደሆነ ማረጋገጥ ችለናል።
‘ፕሮፍ ፀጊ ነኝ’ የሚል ስም ባለዉ የፌስቡክ ገጽ የተጋራ ምስልም በተመሳሳይ መልኩ በሰው ሰራሽ አስተውሎት የተሰራ መሆኑን ሃይቭ ሞደሬሽን ድረ-ገጽን በመጠቀም ባደረግነዉ ማጣራት አረጋግጠናል።
ስለሆነም እነዚህ ምስሎች ትክክለኛ ካለመሆናቸው በተጨማሪ ይዘቶቻቸዉ ለተሳሳተ መረጃ ሊያጋልጡን ስለሚችሉ መሰል ምስሎችን ከማመናችን እንዲሁም መልሰን ከማጋራታችን በፊት ተገቢዉን ማጣራት እናድርግ።
ኢትዮጵያ ቼክ

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::