አልፋሽጋ በኢትዮጵያ ቁጥጥር ስር ገባ በሚል የተሰራጨው መረጃ የተሳሳተ መሆኑን የሚጠቁም መረጃ በመንግስት ተሰጠ

አልፋሽጋ በኢትዮጵያ ቁጥጥር ስር ገባ በሚል የተሰራጨው መረጃ የተሳሳተ መሆኑን የሚጠቁም መረጃ በመንግስት ተሰጠ

ሐምሌ 3፣ 2017

ኢትዮጵያ እና ሱዳን በሚዋሰኑበት ድንበር ላይ በሚገኘው ‘አልፋሽጋ’ በተባለ ስፍራ ዙርያ የተለያዩ መረጃዎች ማህበራዊ ሚድያ ላይ ከሰሞኑ ሲዘዋወሩ ተመልክተናል።

በዚህ ዙርያ በዛሬው እለት ለሚድያዎች ማብራርያ የሰጡት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ነቢያት ጌታቸው መረጃው የተሳሳተ መሆኑን የሚጠቁም መረጃ አቅርበዋል።

”ከሱዳን ጋር በተያያዘ የተነሳው ከዚህ ከአልፋሽጋ ወይም ውሀመስክ ከሚባለው አካባቢ ጋር በተያያዘ እንቅስቃሴዎች እንዳሉ ሚዲያ ላይ አብረን ነው ያየነው። በመንግሥት በኩል የተለየ እንቅስቃሴ እንደሌለ ለመግለፅ እወዳለሁ” በማለት አምባሳደር ነቢያት ምላሽ ሰጥተዋል።

በዚህ ዙርያ ከስድስት ቀን በፊት ሱዳን ትሪቢዩን የተባለ ሚድያ በሰራው ዘገባ በኢትዮጵያ መንግስት የሚደገፉ ሚሊሺያዎች ወደ አልፋሽጋ ገብተው እንደነበር ቢጠቅስም አልፋሽጋን ተቆጣጠሩት የሚል መረጃ አላቀረበም: https://sudantribune.com/article302566/#google_vignette

አብዛኛዎቹ ሚድያዎች እና የሶሻል ሚድያ ገፆች ይህን የሱዳን ትሪብዩን ዘገባ እንደተጠቀሙ ዳሰሳችን ያሳያል። ይሁንና ዘገባው ላይ የተጠቀሱት የምስራቅ ሱዳን አስተባባሪ ኮሚቴ ምክትል ፕሬዝደንት ሙባረክ አል-ኑር የኢትዮጵያ ሀይሎች ጥሰው ገብተው ቦታ ማፅዳት እንደጀመሩ ቢናገሩም አልፋሽጋ የተባለውን ሰፊ ለም መሬት በኢትዮጵያ ቁጥጥር ስር ስለመግባቱ አልተናገሩም።

ጥቅምት 24/ 2013 ዓ.ም የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ሲቀሰቀስ ኢትዮጵያ በአርሶ አደሮቿ ይዞታ ስር ከነበሩት እና ሱዳን ይገባኛል ከምትለውና በሠራዊቷ ከሚጠበቀው አወዛጋቢ የድንበር አካባቢ ወታደሮቿን ማስወጣቷን ተከትሎ ሱዳን ቦታውን በኃይል ተቆጣጥራ መቆየቷ ይታወሳል።

ኢትዮጵያ ከእነዚህ ግዛቶች ሱዳን ጦሯን እንድታስወጣ በተደጋጋሚ ብትጠይቅም ሱዳን ግን የቀደሙ ግዛቶቼን ነው ያስመለስኩት በሚል እንደማትወጣ አስታውቃለች።

ኢትዮጵያ ቼክ!

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::