መረጃን በማጣራት ስራ ስኬታማው ፖሊቲፋክት ምን ያስተምረናል? 

ግዜው እ.ኤ.አ. በ2009 ዓ.ም. ነበር። ከተመሰረተ 2 ዓመት እንኳን ያልሞላው ፖሊቲፋክት የተባለ የመረጃ አጣሪ ቡድን የፑሊትዘር ሽልማትን (Pulitzer Prize) ብዙዎችን ባስደነቀ መልኩ ተሸልሞ ነበር። አምስት ጋዜጤኞች እና አርታኢዎችን ጨምሮ ጥቂት ተመራማሪዎችን የያዘው ይህ ቡድን በቀድሞ ስሙ ሴይንት ፒተርስበርግ ታይምስ በሚባል ጋዜጣ ውስጥ የ2008 (እ.ኤ.አ.) የአሜሪካ ምርጫን ምክንያት አድርጎ የተፈጠረ የዘገባ ፕሮጀክት ነበር። 

ቡድኑ በዚህ ጊዜ ውስጥ በአሜሪካውያን ፖለቲከኞች የተነገሩ ከ750 በላይ ንግግሮችን አጣርቶ እውነቱን ከውሸት፣ ፍሬውን ከገለባ በመለየቱ ነበር ይህንን የከበረ ሽልማት የተሸለመው። እነዚህ ጋዜጠኞች የመረጃ ማጣራት ስራውን ሲጀምሩ ታድያ ነገሮች ቀላል እንደማይሆኑ ያውቁ ነበር። ምንም እንኳን የጋዜጠኞቹ ፕሮጀክት በፍሎሪዳ ግዛት ትልቁ የሚባለው ጋዜጣ በባለቤትነት የሚያስተዳድረው ቢሆንም፣ ከሁሉም አቅጣጫ ቁጣን እንደሚያስተናግዱ ምንም አልተጠራጠሩም። ቶሎ ብለውም ትኩረትን ማግኘት ነበረባቸው። 

በጥቂት ጋዜጠኞች እና ተመራማሪዎች የተመሰረተው ይህ የመረጃ ማጣራት ፕሮጀክት ትኩረት ማግኘት የጀመረው ’የሀቅ-መለኪያ’ (Truth-o-Meter) የሚል ስም በተሰጠው በዓይነቱ ልዩ በሆነ የደረጃ አሰጣጥ ሂደት፣ እነዚህን ንግግሮች ‘እውነት’፣ ‘እንደነገሩ እውነት’፣ ‘ግማሽ ውሸት’፣ እና ‘ውሸት’ በሚል መመደብ ከጀመረ በኋላ ነበር። 

በሀገራችን ኢትዮጵያ ውስጥም ይህንን ስራ መስራት የሚችሉ ሰፊ ልምድ ያላቸው ጋዜጠኞች እና የሚድያ ተቋማት እንዳሉ ይታወቃል። የፖሊቲፋክትን ምርጥ ተሞክሮ በኢትዮጵያ አውድ ውስጥ ለመተግበር ቀጠሮ መያዝም አያስፈልግም። 

ከነዚህ በጣት የሚቆጠሩ ግለሰቦች ከመሰረቱት ፕሮጀክት (አሁን ራሱን የቻለና ተጽዕኖ ፈጣሪ ከሆነ ድርጅት) ብዙ ልምድ ማግኘት እንችላለን። ዘግይቶም ቢሆን ጥቂት መረጃ የማጣራት ስራዎችን የሚሰሩ ተቋማት በሀገራችን ብቅ ማለታቸው ጥሩ ቢሆንም፣ ከዚህ በበለጠ መስራት እንደሚቻል ግን እሙን ነው።  

አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ የሀሰተኛ መረጃ ስርጭትን መግታት በይደር የማይተው ስራ ነው። በይደር የማይተው ስራ መሆኑ ላይ ብዙዎች የሚስማሙበት አንዱ ምክንያት አፍራሽ የሆነ አዙሪት ውስጥ ሊከተን የሚችል ጉዳይ በመሆኑ ነው። 

ሌሎችን ማሳመን የሚጠይቁ ስራዎችን የሚሰራ ማንኛውም ሰው አንድን እውነታ የማዛባት፣ የማጋነን ወይም የመሸፈን ገፊ ምክኒያት አለው፣ ሰበብ ሊባልም ይችላል። አዙሪቱ ታዲያ ያለው እዚህ ላይ ነው: በዚህ ሀሰተኛ ይዘት ምክንያት የተፈጠረውን ‘የሃይል መዛባት’ ማስተካከል በሚል ሌላ ገፊ ምክኒያት ሌላ ሀሰት የሆነ ይዘት ይፈጠራል። 

እንዲያ እንዲያ እያለ ማለቂያ ወደሌለው ዓለም – የውሸት፣ የቅጥፈት፣ የጥፋት ዓለም – ጉዞ ይጀመራል። ለዚህ ነው የሀሰተኛ መረጃ ስርጭትን መግታት ለነገ የሚባል ስራ አይደለም የሚባለው/የምንለው።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::