በማህበራዊ ሚዲያ የሚሰራጩ የጥላቻ ንግግሮች የሚያድርሱትን ጉዳት ለመቀነስ በግለሰብ ደረጃ ምን ማድረግ እንችላለን? 

የጥላቻ ንግግር መሬት ወርዶ በማህበረሰቦች መካከል አለመተማመን፣ ግጭት ብሎም የእርስ በርስ ጦርነት እንደሚፈጥር እውነት ነው። የማህበራዊ ሚዲያ ፕላትፎርሞች ደግሞ ለጥላቻ ንግግር አራማጆች ምቹ መድረክ ስለመሆናቸው ብዙዎቹ ይናገራሉ። በየዕለት ከዕለት የማህበራዊ ሚዲያ መስተጋብራችንም ይህን መታዘብ ይቻላል። 

ሆኖም በየዕለቱ የማህበራዊ ሚዲያ መስተጋብራችን ላይ የሚከተሉትን በጎ እርምጃዎች ብንወስድ የጥላቻ ንግግር የሚያደርሰውን አሉታዊ ተጽዕኖ በእጅጉ መቀነስ እንችላለን። 

መታቀብ:

በማህበራዊ ሚዲያ አካውንቶቻችን ብሔር፣ ዘርን፣ ሀይማኖት፣ ጾታን፣ አካል ጉዳተኝነትን መሰረት ያደረገና መድሎን ወይም ጥቃትን የሚያነሳሳ የጥላቻ ንግግር ከማጋራት በመታቀብ በጎ አስተዋጾ ማበርከት እነችላለን። የጥላቻ ንግግሮች በማህበራዊ ፕላትፎርሞች ሲያጋጥሙን ‘ላይክ’፣ ‘ሼር’ ወይም ንግግሩን የሚያበረታታ አስተያየት አለመስጠትም እንዲሁ። 

መቃወም:

በማህበራዊ ሚዲያ የጥላቻ ንግግር ስንመለከት ዝም ማለት ድርጊቶን እንደማበረታታ ሊቆጠር ይችላል። ይልቁንስ እንዲህ ያሉ ድርጊቶችን ስንመለከት በመቃወምና በማጋለጥ በጎ አስተዋጾ ማበርከት እንችላለን። ምላሻችንም በእውነትና በእውቀት ላይ የተመሰረት እንዲሁም ስሜት ያልተጫነው ሊሆን ይገባል። 

መደገፍ:

የማህበራዊ ሚዲያ አካውንቶቻችንን በመጠቀም የጥላቻ ንግግር ሰላባ የሆኑ ማህበረሰቦችና ግለሰቦች መደገፍና ከጎናቸው መቆም ሌላኛው በቀላሉ ማድረግ የምንችለው በጎ አስተዋጾ ነው። ይህም የጥላቻ ንግግር አዙሪትን ለመስበር የሚያግዘን ሲሆን በተጨማሪም ከጥላቻ ንግግር አራማጆች ጎን አለመቆማችንን ማሳየት እንችላለን። 

ሪፖርት ማድረግ:

አብዛኞቹ የማህበራዊ ሚዲያ አገልግሎት ሰጭ ፕላትፎርሞች የጥላቻ ንግግርን በፖሊሲ ደረጃ የሚከለክሉ ሲሆን እንዲህ ያሉ ድርጊቶች ሪፖርት የሚደረጉባቸው ቀለል ያሉ ስርዐቶች አሏቸው። እኛም የጥላቻ ንግግር ስንመለከት ሪፖርት በማድረግ የድርጊቱ አራማጆች በፕላትፎርሞቹ ቦታ እንዳይኖራቸው ማድረግና ተጽኗቸውን መቀነስ እንችላለን። 

መሳተፍ:

የጥላቻ ንግግር ስርጭትን ለመግታት እንቅስቃሴ የሚያደርጉ የማህበራዊ ሚዲያ ቡድኖችን (social media groups) በማቋቋምና በመቀላቀል ስለድርጊቱ የማንቃት ስራ በመስራት በጎ አስተዋጾ ማበርከት እንችላለን። እንዲህ ያሉ የማህበራዊ ሚዲያ ቡድኖችን ማቋቋም፣ መቀላቀል እንዲሁም መሳተፍ ስለጥላቻ ንግግር ለማስተማርና ለማንቃት ብሎት በቀላሉ ሸብረክ የማይል ማህበረሰብ ለመፍጠር በእጅጉ ይረዳል። 

የራሳችንን በጎ አስተዋጾ በማበርከት በማህበራዊ ሚዲያ የሚሰራጩ የጥላቻ ንግግሮች የሚያድርሱትን ጉዳት እንቀንስ!

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::