ሴራ ትንተና ምንድን ነው? ለሀሰተኛ መረጃ ስርጭትስ ምን አስተዋፅዖ እያረገ ይገኛል?

ከኢንተርኔት መስፋፋት ጋር ተያይዞ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ከመጡ ክስተቶች መካከል የሴራ ትንተና ወይንም በእንግሊዘኛ ስያሜው ኮኒስፓይሬሲ ቲዎሪ ( conspiracy theory) አንዱ ነው።በሺዎች የሚቆጠሩ ድረ-ገጾች፣ የማህበራዊ ሚዲያ ገጾች እንዲሁም የዩቲዩብ ቻናሎች በየቀኑ ብዛትያላቸው በሴራ የተለወሱ ይዘቶችን ያሰራጫሉ።

የአንዳንዶቹ ገጾች እና ቻናሎች አዘጋጆች በርከት ያሉ ተከታዮችን ማፍራት የቻሉ ሲሆን በሚሊዮን ኮፒ የተሸጡ የሴራ መጻህፍትንም ለህትመት አብቅተዋል። ከነዚህ መካከል የተወሰኑት በአማርኛ ቋንቋ ተተርጉመዋል። የመጻህፍቶቹ ይዘትም በአብዛኛው ‘ኢሊሙናቲ’ እና ወዘተ ተብለው ከሚጠሩ የህዑእ ቡድኖች ላይ ያጠነጥናል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን በፖለቲካ፣ በጤና እና በሌሎች ጉዳዮች ላይ የሴራ ትንታኔ ዝንባሌ ያላቸው ይዘቶችን የሚያዘጋጁ ሀገርኛ ገጾች እና ቻናሎች መበራከታቸውን ተመልክተናል። የሴራ ትንታኔ ዝንባሌ ያላቸው ሀገርኛ ይዘቶች በስፋት ከሚሰራጩባቸው ፕላትፎርሞች ዩቲዩብ በቀዳሚነት ሊጠቀስ የሚችልሲሆን በተንታኝነት የሚቀርቡ ግለሰቦች ስለፖለቲካ፣ ስለ አለም አቀፍ ግንኙነት፣ ስለጤና (በተለይም ስለኮቪድ ወረርሽኝና መከላከያ ክትባቶች) ወዘተ ትንታኔዎችንና መረጃ ነው የሚሉትን ማስረጃ ሲያቀርቡ ይደመጣል።

የሴራ ተንታኞች ለሚከሰቱ ክስተቶች ወይንም ድርጊቶች በአመክንዮ ወይንም በተጨባጭ መረጃ የተደገፈ ትንታኔ እና ዘገባ ከማቅረብ ይልቅ መጥፎ አላማ ያላቸው በህብዑ የተደራጁ ቡድኖች ወይንም ግለሰቦች እጅ አለበት ብለው ማመናቸው መለያ ባህሪያቸው ነው። ግለሰቦችን ወይንም ማህበረሰቦችን መጥፎ እና ጥሩ በማለት መከፋፈል ሌላው መለያቸው ሲሆን በዚህም በቡድኖችና በማህበረሰቦች መካከል ያለውን የፖለቲካ ወይንም ሌላ ልዩነት የማይታረቅ አድርገው በማቅረብ ልዩነትንና መካረርን ማስፋት ሌላው መለያቸው ነው። ለሚፈጠሩ አሉታዊ ክስተቶችና ድርጊቶች በጠላትነት የፈረጁትን ግለሰብ ወይንም ቡድን ማምለጫ (scapegoat) ማድረግም የሴራ ተንታኞች የተለመደ ባህሪ ነው።

ሴራ ተንታኞች ለሚያቀርቡት ትንታኔ ወይንም ዘገባ ጥርጣሬ መንደርደሪያቸው ሲሆን ጥርጣሬያቸውን እውነት ለማድረግ ማንኛውንም ማስረጃ እንደመረጃ እንዲወሰድ ላይ ታች ማለታቸው የተለመደ ነው። በዚህም በቀላሉ ብዙ ተከታይ ማፍራት የሚችሉ ሲሆን የሴራ ትንታኔያቸው ወደ ህብረተሰቡ ከሰረገ በኃላ ስርጭቱን ለማቆም አስቸጋሪ ይሆናል። ጥቂት በማይባሉ ዜጎች ላይ የኮቪድ 19 መከላከያ ክትባትን ለመከተብ የታየው ማፈግፈግ ለዚህ አንድ ምሳሌ ሊሆን ይችላል።

ይህን በዜጎች መካከል ጥርጣሬን፣ መከፋፈልን፣ ጥላቻን ብሎም ግጭትን የሚፈጥር እንዲሁም ሳይንሳዊና ተጨባጭ መረጃዎችን የሚቃረን የሴራ ትንታኔ ድርጊት መስፋፋትን ለመግታት አስቸጋሪ ቢሆንም የሚከተሉትን ጥንቃቄዎች ማድረግ እንደመፍትሄ ሊወሰድ ይችላል።

የመጀመሪያው መፍትሄ በዩቲዩብ ወይንም በሌሎች ፕላትፎርሞች ትንታኔ የሚሰጡ ግለሰቦች በጉዳዩ ላይ በቂ እወቀት ወይንም ሙያ እንዳላቸው መጠየቅ ነው። ትንታኔ የሚያቀርበው ግለሰብ በጉዳዩ ላይ በቂ የሙያ ማረጋገጫ ወይንም እወቅት ከሌለው ለሴራ ትንታኔ ሊያጋልጥዎ ይችላል። ለቀረበው ዘገባ ወይንም ትንታኔ ተጨባጭ መረጃ ወይንም በሳይንስ የተደገፈ ዳታ መቅረቡንና አለመቅረቡን መጠየቅ ሌላኛው እራሳችንን ከሴራ ትንታኔ ለመከላከል የሚረዳን ዘዴ ነው። በተንታኝነት የቀረበው ግለሰብ ለሚያቀርበው ጉዳይ በግልጽ የሚታወቅ የመረጃ ምንጭ ማቅረብ ካልቻለ ጥንቃቄ ያድርጉ። በተጨማሪም በተንታኙ ወይንም በዘገባው የቀረበው ጉዳይ በአንጻራዊነት ታማኝነት ባለቸው ሚዲያዎች ወይንም በመረጃ አጣሪ ተቋማት ስለመቅረቡ ያጣሩ።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::