ክሊክ አጥማጆች (clickbaits) ምንድን ናቸው?

የፖለቲካ አለመረጋጋት ወይንም ግጭት ሲኖር በየሰዐቱ የሚፈጠሩ ክስተቶችን ለማወቅ ጉጉታቸን ይጨምራል። የማወቅ ጉጉታችንን ለማርካት መረጃ ልናገኝባቸው እንችላለን ያልናቸውን የማህበራዊ ሚዲያ ገጾች ወይንም ቻናሎች አልያም ሚዲያዎች ማሰሳችን ይጠበቃል። በአሰሳችን ወቅት ለክሊክ አጥማጆች (clickbaits) የመጋለጥ እድልም ይኖረናል።

የክሊክ አጥማጆች ለስሜታችን የቀረበ፣ ጉጉት የሚያጭር፣ “አትለፉኝ አትለፉኝ” የሚል የዜና ርዕስ (headline) እና በደንብ የተቀናበረ ፎቶ በመጠቀም ማስፈንጠሪያዎችን እንድንከተል ወይንም ቪዲዮዎችን እንድንከፍት የሚገፋፉ ገጾችና ቻናሎች ሲሆኑ ወደ ውስጥ ገብተን ይዘታቸውን ስንመለከት ከዜና ርዕሳቸው ጋር የማይገናኝ፣ ምንጭ የሌለው፣ ከዚህም ከዚያም የተቃረመ ሆኖ እናገኘዋለን።

ክሊክ አጥማጆች በኢትዮዮጵያ በተለይ በዩትዩብ በርከት ብለው የሚገኙ ሲሆን አብዛኞቹ አላማቸው ብዙ ሰብስክራይበርና ተመልካች በማግኘት ብር ማግኘት ሲሆን ሌሎቹ የፖለቲካ አላማቸውን ለማሳካት ይጠቀሙበታል።

ክሊክ አጥማጆች በአብዛኛው ይዘታቸው ምንጭ የማይጠቅስ፣ የተጋነነ፣ ርዕታዊነት የጎደለውና ወገንተኛ ሆኖ ይገገኛል። በዚህም ለሀሠተኛና የተዛቡ መረጃው ስርጭት ከፍተኛ ድርሻ ይወስዳሉ።

ስለሆነም በክሊክ አጥማጅ የዩቲዩብ ቻናሎች ወይንም ድረ-ገጾች የሚቀርቡ መረጃዎችን ከማመናችን እና ከማጋራታችን በፊት ቆም ብሎ ማሰብ እና የሚከተሉትን ጥያቄዎች መጠየቅ በሀሰተኛና የተዛባ መረጃ ከመጋለጥ ይታደጋል:

* የመረጃ አቅራቢው ሚዲያ ወይንም ግለሰብ ማንነት ይታወቃል?
* መረጃ አቅራቢው ለድርጊቱ ወይንም ድርጊቱ ለተፈጸመበት አካባቢ ምን ያህል ቅርብ ነው?
* መረጃ አቅራቢው ታማኝ ምንጭ ጠቅሷል?
* መረጃውን በአንጻራዊነት ታማኝ የሆኑ የሚዲያ ተቋማት ዘግበውታል?
* መረጃ አቅራቢው መረጃውን በፎቶ ወይንም በቪዲዮ አስደግፏል?
* ፎቶዎች እና ቪዲዮዎች ትክክለኛ እና እውነተኛ ናቸው?

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::