ፎቶዎችና ተንቀሳቃሽ ምስሎች የተወሰዱበትን ትክክለኛ ቦታና ጊዜ ለማወቅ የሚረዱ መገልገያዎች! 

በየዕለቱ በርከት ያሉ ፎቶዎችንና ተንቀሳቃሽ ምስሎችን በማህበራዊ ሚዲያ ገጾችና ቻናሎች እንዲሁም በቴሌቪዥንና በህትመት ውጤቶች እንመለከታለን። እነዚህ ፎቶዎችና ተንቀሳቃሽ ምስሎች ተነሱ ወይንም ተቀረጹ የተባለበት ቦታና ጊዜ ሁልጊዜ እውነተኛ ላይሆን ይችላል። ለዚህም ፎቶዎችና ተንቀሳቃሽ ምስሎች የተወሰዱበትን ትክክለኛ ቦታና ጊዜ ለማወቅ የሚረዱ መገልገያዎችን መጠቀም ሀሠተኛና የተዛቡ መልዕክቶችን ለማረቅ ይረዳል። 

ኢትዮጵያ ቼክ በዛሬው የሰኞ መልዕክት ፎቶግራፎችና ተንቀሳቃሽ ምስሎች የተነሱበትን ወይንም የተቀረጹበተን ትክክለኛ ቦታና ጊዜ ለመለየት (Geolocation) የሚረዱ የጎግል የካርታ አገልግሎት (Google Maps) እና ሰንካልክ (Suncalc) የተሰኙ ሁለት መገልገያዎችን ያስተዋውቃል። 

1. የጎግል ካርታ (Google Maps):- ይህ መገልገያ በርከት ያሉ አገልግሎቶችን የሚሰጥ ሲሆን የሳተላይት ምስል (Satelite Images) እና የመንገድ እይታ (Street View) አገልግሎቶቹ ፎቶዎችና ተንቀሳቃሽ ምስሎች የተነሱበትን ትክክለኛ ቦታን ለመለየት ይረዳሉ። የጎግል ካርታን በመጠቀም ፎቶግራፎችና ተንቀሳቃሽ ምስሎች የተነሱበትን ወይንም የተቀረጹበትን ትክክለኛ ቦታና ጊዜ ለመለየት በመጀመሪያ ምስሎቹን በአንክሮ ደጋግሞ መመልከት ይጠይቃል። ይህም በምስሉ ላይ ጎላ ብለው የሚታዩ የማመሳከሪያ ምልክቶችን ወይንም ፍንጮችን ለመለየት ያስችላል። ከነዚህ መካከል የመልክዐ ምድር አቀማመጥን (ተራሮች፣ ጉብታዎች፣ ወንዞች፣ ሜዳዎች ወዘተ)፣ የዕጽዋት ሽፋንን፣ የህንጻዎች አይነትን (ስፋት፣ ርዝመት፣ ቀለም ወዘተ)፣ አደባባዮችን፣ የንግድ ወይንም የድርጅት ስሞችን የሚያሳዩ የማስታወቂያ ሰሌዳዎችን እንዲሁም ቋንቋን መጥቀስ ይቻላል። የሳተላይ ምስሎች ለማጣራት የምንፈልገው ምስል የተወሰደበትን ቦታ ከላይ በግልጽ ለማየት የሚያስችሉ ሲሆን ከማመሳከሪ ምልክቶችና ፍንጮች ጋር በማነጻጸር ፎቶግራፎችና ተንቀሳቃሽ ምስሎች የተወሰዱበትን ትክክለኛ ቦታ ማወቅ ይቻላል። የጎዳና እይታ አገልግሎቱ ደግሞ የማመሳከሪያ ምልክቶችንና ፍንጮችን በአግድም እንድናይ በማስቻል ምስሎቹ የተወሰዱበትን ቦታ ለመለየት ይረዳል። 

2. ሰንካልክ (Suncalc):- በፀሐይ እንቅስቃሴ ላይ በመመርኮዝ ፎቶዎችና ተንቀሳቃሽ ምስሎች የተወሰዱበትን ትክክለኛ ቀንና ሰዐት ለመለየት የሚያስችል መገልገያ ነው። ይህን ለመለየት መገልገያው በፎቶዎችና በተንቀሳቃሽ ምስሎች ላይ የሚታዩ የጥላ አቅጣጫዎችንና ርዝመቶችን እንደማመሳከሪያ ይጠቀማል። ሰንካልክን ለመጠቀም በመጀመሪያ ምስሎቹ የተወሰዱበትን ትክክለኛ ቦታ ማወቅ ይጠይቃል።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::