የተነካኩ ፎቶዎችን ለመለየት የሚረዱ መገልገያዎች!

ኢትዮጵያ ቼክ ከመረጃ ማንጠር አገልግሎቱ ጎን ለጎን ዜጎች የሚዲያ ንቃታቸው ከፍ እንዲል የሚያግዙ ትምህርታዊ መልዕክቶችን እንዲሁም መረጃን ለማንጠር የሚረዱ ዘዴዎችንና መገልገያዎችን ዘወትር ሰኞ ሲያስተዋውቅ ቆይቷል። ዛሬ የተነካኩ ፎቶዎችን (manipulated photos) ለመለየት የሚረዱ ሶስት መገልገያዎችን ያስተዋውቃል።

1.      ፎቶፎረንሲክስ (Fotoforensics)

ፎቶፎረንሲክ በብዙዎች ዘንድ ተመረጭ የሆነ የተነካኩ ምስሎችን በቀላሉ ለመለየት የሚረዳ መገልገያ ነው። ይህ መገልገያ የተነካኩ ፎቶዎችን ለመለየት የተለያዩ የምርመራ ዘዴዎችን በመጠቀም ውጤቶችን ያቀርባል።

ከምርመራ ዘዴዎች አንዱ የስህተት ህዳጎችን (Error level analysis) ለመለየት የሚያስችል ሲሆን ውጤቱንም ቀለሞችን በመጠቀም ያሳውቃል። ለምሳሌ ለምርመራ የቀረበው ፎቶ የተነካካ ከሆነ፣ የተነካካው ቦታ ላይ ደማቅ ቀለሞችን ያሳያል። በአንጻሩ ለምርመራ የቀረበው ምስል ያልተነካካ ከሆነ፣ የምርመራውን ግኝት የሚያሳየው ምስል ነጭ፣ ጥቁር አልያም ግራጫ ቀለሞችን ይጠቀማል።

ከዚህ በተጨማሪ ፎቶፎረንሲክስ ለምርመራ የቀረበውን ፎቶ አከመቻቸት (JPEG) እና ሜታ ዳታ (Meta Data) በማሳየት ተጠቃሚዎች የተነካኩ ፎቶዎችን በቀላሉ እንዲለዩ ይረዳል። ለምሳሌ ለምርመራ የቀረበው ፎቶ የአከመቻቸት ውጤት በፐርሰንት የሚገለጽ ሲሆን ፎቶው ዝቅተኛ ፐርሰት ካስመዘገበ ተነካክቷል ማለት ነው።

2.    ኢሜጅ ኤዲትድ ፎቶሾፕ አናላይዘር (Image Edited Photoshop Analyzer)

ይህ መገልገያ የተነካኩ ፎቶዎችን ለመለየት የተለያዩ ዘዴዎችን ይጠቀማል። ከፎቶፎረንሲክ አንጻር ኢሜጅ ኤዲትድ ፎቶሾፕ አናላይዘር ለምርመራ የቀረበለትን ፎቶ ከተመለከተ በኃላ ውጤቱን ግልጽ በሆነ ቋንቋ “አዎ” ወይንም “አይ”ይበማለት ያሳውቃል።

በተጨማሪም ፎቶው የተነካካ ከሆነ፣ የኢሜጅ ኤዲትድ ፎቶሾፕ አናላይዘር መገልገያ ፎቶውን ለመነካካት  ጥቅም ላይ የዋለውን ሶፍትዌር ያሳውቃል።

3.    ፎረንሲካሊ ፎቶሾፕ አናላይዘር (Forensically Photoshop Analyzer)

ከላይ እንደተጠቀሱት ሁለት መገልገያዎች ሁሉ ፎረንሲካሊ ፎቶሾፕ አናላይዘርም የተነካኩ ፎቶዎችን ለመለየት የተለያዩ የምርመራ ዘዴዎችን ጥቅም ላይ ያውላል። ነገር ግን ተጠቃሚዎች አጉሊ መነጸርን (magnifying glass) በመጠቀም የተነካኩ ፎቶዎችን እንዲለዩ የሚያስችለው አገልግሎቱ ለየት ያደርገዋል። ይህ አገልግሎት ለአጠቃቀም ግልጽና ምቹ ሲሆን ተገልጋዮች በቀላሉ በፎቶው ላይ የተነካኩ ቦታዎችን እንዲለዩ ይረዳል።

ከዚህ በተጨማሪ ፎረንሲካሊ የስህተት ህዳግ፣ የሜታዳታ እና ሌሎች የምርመራ ዘዴዎችንም ጥቅም ላይ ያውላል።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::