ሀሰተኛ ምስሎችን እና አካውንቶችን ለመለየት የሚያግዙ መተግበርያዎች!

በየዕለቱ በማህበራዊ ሚድያዎች በርከት ያሉ መረጃዎች ይሰራጫሉ። ከሚሰራጩ መረጃዎች መካከል የተወሰኑት ሀሰተኛ ወይንም የተዛቡ ሊሆኑ ይችላሉ። የመረጃዎችን ትክክለኛነት ለማወቅ የመረጃ አንጣሪ ገጾችን ወይንም በአንጻራዊነት እውነተኛ መረጃ ያሰራጫሉ ተብለው የሚታመኑ ሚዲያዎችን መጎብኘት አንድ አማራጭ ነው።

ሌላኛው አማራጭ ሀሰተኛና የተዛቡ መረጃዎችን ለመለየት የሚያስችል የሚዲያ ንቃት (media literacy) መፍጠር ነው።

ኢትዮጵያ ቼክ ዜጎች የሚዲያ ንቃታቸውን እንዲያጎለብቱ የሚረዱ ጠቃሚ መገልገያዎችን (apps) እና መተግበሪያዎችን (tools) ከዚህ በፊት ማስተዋወቁ ይታወቃል። ዛሬ ሁለት ተጨማሪ መተግበሪያዎችን እናስተዋውቃለን።

1. Forensically

በማህበራዊ ትስስር ገጾች ከሚደርሱን ፎቶዎች አንዳንዶቹ ከአውድ ውጭ የቀረቡ ሊሆኑ ይችላሉ። ይህን ለመለየት ‘Reversee’፣ ‘Tineye’፣ ‘Google reverse image search’ ወይንም ሌሎችን የሪቨርስ ኤሜጅ መፈለጊያ መተግበሪያዎችን በመጠቀም በቀላሉ መለየት ይቻላል።

ፎቶዎችን በሪቨርስ ኤሜጅ መፈለጊያ መተግበሪያዎች በመጠቀም ማግኘት ካልቻልን ምናልባት ፎቶሾፕ ተሰርተው ሊሆን ይችላል። በፎቶሾፕ የተቀናበሩ ፎቶዎችን ለመለየት ከምንጠቀምባቸው መገልገያዎች መካከል ‘Forensically’ አንዱ ሲሆን ፎቶዎችን አጉልቶ በማሳየት የተነካኩ ቦታዎችን በቀላሉ ለማወቅ ያስችላል። ከ’Forensically’ በተጨማሪ ‘Amped Authenticate’ እና ‘FotoForensics’ እነዚህን ፎቶዎች ለመለየት የሚረዱ መገልገያዎች ናቸው።

2. Botometer

ይህ መገልገያ የትዊተር አካውንቶች ቦት (bot) ወይንም ሰው ስለመሆናቸው ለመየት ይረዳል። መገልገያው ውሳኔ ላይ ለመድረስ የአካውንቱን የማህበራዊ ትስስር አወቃቀር (social network structure)፣ የየዕለት ክንውን፣ የቋንቋ አጠቃቀም ወዘተ ያጠናል። በዚህም ለአካውንቶቹ ከ0 እስከ 5 ነጥብ ይሰጣል። ነጥቡ ከፍተኛ ከሆነ አካውንቱ ቦት የመሆን ዕድሉ የሰፋ ይሆናል።

በየዕለቱ የሚዲያ ንቃትን በማጎልበት እንዲሁም እውነትን ከሀሰት ለመለየት የሚያስችሉ መተግበሪያዎችን እና መገልገያዎችን አጠቃቀም በማወቅ ሀሰተኛና የተዛቡ መረጃዎች የሚያደርሱትን አሉታዊ ተጽዕኖ መቀነስ ይቻላል።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::