በአስደንጋጭ ሁኔታ እየተስፋፋ ላለው የኮቪድ-19 ስርጭት የሀሰተኛ መረጃዎች እና ሴራ ትንተናዎች አስተዋፅኦ እያደረጉ ነው!

የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በመላው ዓለም እያስከተለ ያለው ቀውስ አሁንም መቀጠሉን የዓለም የጤና ድርጅትን ጨምሮ ሌሎች የሚመለከታቸው የጤና ተቋማት የሚያወጧቸው ሪፖርቶች ያሳያሉ። የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ከቀናት በፊት ያወጣው መግለጫም የኮቪድ-19 ወረርሽን በሀገራችን በፍጥነት በመዛመት ላይ መሆኑን ይጠቁማል።

ኢንስቲትዩቱ ታህሳስ 22/2014 ዓ.ም ያጋራው መረጃ እንደሚያሳየው በአዲስ አበባ በተለያዩ ተቋማት በተደረገ የመስክ ቅኝትና በተወሰደ የናሙና ምርመራ ከ59 እስከ 86 በመቶ የሚሆኑ ሰዎች ኮቪድ-19 የተገኘባቸው ሲሆን በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ ወደ ጤና ተቋማት ሄደው ምርመራ ከተደረገላቸው 55,562 ሰዎች ውስጥ ደግሞ 25,191 ያህሉ ቫይረሱ እንዳለባቸው ተረጋግጧል።

በተጨማሪም በሀገር አቀፍ ደረጃ በኮቪድ የመያዝ ምጣኔ ከሁለት ሳምንት በፊት ከነበረው 5 በመቶ አንጻር በታህሳስ 21/2014 ዓ.ም ወደ 36 በመቶ ከፍ ብሏል። ይህም በሀገራችን “አዲስ የኮቪድ-19 ወጀብ መከሰቱን” እንደሚያሳይ የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ይፋ አድርጓል።

ይህንን አሳሳቢ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ስርጭት ለመግታት ህብረተሰቡ የመከላከያ መንግዶችን ያለመሰልቸት ከመተግበር በተጨማሪ የመከላከያ ክትባቶችን መውስድ እንዳለበት የጤና ባለሙያዎች አሁንም በማሳሰብ ላይ ይገኛሉ።

ምንም እንኳን በበለጸጉና በማደግ ላይ ባሉ አገሮች መካከል ከፍተኛ የሆነ የኮቪድ-19 መከላከያ ክትባት አቅርቦት ልዩነት መኖሩን መረጃዎች ቢያሳዩም ክትባት ለመከተብ ማመንታት ወይም አለመፈልግ የወረርሽኙን ስርጭት ለመግታት ለሚደረገው ጥረት እንደ ተግዳሮት ይወሳደል።

ለምሳሌ የአፍሪካ የበሽታ መቆጣጠሪያ እና መከላከያ ማዕከል (Africa CDC) ከሳምንት በፊት ያወጣው መረጃ እንደሚያሳየው በአፍሪካ ከተሰራጩ 543.2 ሚሊዮን የኮቪድ-19 መከላከያ ክትባቶች መካከከል አገልግሎት ላይ የዋሉት 309 ሚሊዮን ብቻ ናቸው፣ ይህም 56.90% ማለት ነው። ኢትዮጵያም እስከ ጥቅምት 24/2014 ዓ.ም 26,409,880 የኮቪድ-19 መከላከያ ክትባቶችን የተረከበች ሲሆን ከዚህ ውስጥ 14,736,068 ክትባቶች ብቻ ጥቅም ላይ ውለዋል።

የኮቪድ-19 መከላከያ ክትባቶችን ለመወሰድ ማመንታት ወይንም አለመፈለግ በመላው ዓለም የተስተዋለ ተግዳሮት ሲሆን ለዚህም ስለክትባቶች የሚሰራጩ ሀሰተኛና የተዛቡ መረጃዎች እንዲሁም የሴራ ትንታኔዎች በዋነኛነት ይጠቀሳሉ።

ስለ ኮቪድ-19 ወረርሽን እንዲሁም ስለመከላከያ ክትባቶቹ ከጤና ተቋማትና ከጤና ባለሙያዎች የሚሰጡ መረጃዎችን በመከታተልና በመተግበር እንዲሁም ከሀሰተኛና ከተዛቡ መረጃዎች፣ ከሴራ ትንታኔዎች በመራቅ የወረርሽኙን ስርጭት ለመግታት በሚደረገውን ጥረት የበኩላችንን አስተዋጽዖ እናበርክት።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::