የሀሠተኛና የተዛባ መረጃ ስርጭትን ለመከላከል ሚድያዎች ሊኖራቸው የሚገባ ሚና!

የሀሠተኛና የተዛባ መረጃ ስርጭት የሚያደርሰውን ዘረፈ ብዙ ችግር በመግታት ረገድ የገለልተኛ የመረጃ አንጣሪ ተቋማት ሚና በግንባር ቀደምነት ይጠቀሳል። ሆኖም ከችግሩ ስፋትና መልከ-ብዙነት አኳያ ከነዚህ ተቋማት በተጨማሪ የሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳትፎ ግድ ይላል፤ በተለይም የሚዲያ ተቋማት።

የሌሎች ሀገራት ልምድ እንደሚያሳየው የሚድያ ተቋማት መረጃን ከማሰራጨት ጎን ለጎን የሀሠተኛና የተዛባ መረጃ ስርጭትን በመከላከል ረገድ ሚናቸው የላቀ ነው። ሚናቸውም ለመረጃ ማንጠር የሚረዱ የተለያዩ መድረኮችን ቀርጾ ተግባር ላይ ከማዋል እስከ የሚዲያ ንቃት መርሀግብሮች ይዘልቃል።

በአሜሪካ ፍሎሪዳ ግዛት የቅድሩስ ፒተርስበርግ ከተማ ዕለታዊ ጋዜጣ ታምፓ ቤይ ታይምስ በዘመናዊ የመረጃ ማንጠር ስራ ፈርቀዳጅ የሆነውን ፖሊቲፋክትን ( PolitiFact) በመጀመር በምሳሌነት ይጠቀሳል። የሀሠተኛና የተዛቡ መረጃዎችን በማጋለጥ በቀዳሚነት ከሚጠቀሱት ፕላትፎርሞች መካከል አንዱ የሆነው የዋሽንግተን ፖስት ፋክት ቼከርም (The Washington Post Fact Checker) የተጀመረው በሌላኛው የአሜሪካ ጋዜጣ ዋሽንግተን ፖስት መሆኑ ይታወቃል። ከዚህ በተጨማሪም ሌሎች የአሜሪካ ጋዜጦች፣ የቴሌቪዥንና የራዲዮ ጣቢያዎች በተቋማቸው ውስጥ የመረጃ አንጣሪ ዴስኮችን በማቋቋም የሀሠተኛና የተዛቡ መረጃዎችን ስርጭት ይዋጋሉ።

የህንድ ሳምታዊ መጽሔት ኢንዲያ ቱዴይ በመጽሔቱና በድረግጹ ሀሠተኛና የተዛቡ መረጃዎችን የሚያጋልጥባቸው ራሳቸውን የቻሉ ገጾች ያሉት ሲሆን የኬኒያው ዴይሊ ኔሽም በኔሽን ኒውስፕሌክስ (Nation Newsplex) ገጹ በዳታ የተደገፈ የመረጃ ማንጠር ስራ ይከውናል። በናይጄሪያና በጋና ራዲዮ ጣቢያዎች የአየር ሰዐት መድበው ሀሠተኛና የተዛቡ መረጃዎችን ያጋልጣሉ።

ወደ ኢትዮጵያ ስንመጣ የሚዲያ ተቋማት ሀሠተኛና የተዛቡ መረጃዎችን በመጋለጥ ረገድ ይህ ነው የሚባል ስራ ሲሰሩ አይታይም። ኢትዮጵያ ቼክ ባደረገው ቅኝት የአየር ሰዐት መድበው ወይንም የጋዜጣ አምድ መድበው መረጃ የማንጠር ስራ የሚሰሩ ሚዲያዎች ማግኘት አልቻለም። በተለይም ሚዲያዎቹ ካላቸው ሰፊ ተደራሽነትና የሰው ሀይል አኳያ የሀሠተኛና የተዛባ መረጃ ስርጭትን ለመግታት የራሳቸውን አስተዋጽዖ ቢያበረክቱ ከፍተኛ ለውጥ ማምጣት ይቻላል።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::