የማህበራዊ ሚድያ ድርጅቶች የሀሰተኛ መረጃ ስርጭትን እና የጥላቻ ንግግርን ለመከላከል ሊወስዷቸው የሚገቡ እርምጃዎች! 

በኢትዮጵያም ሆነ በአለም ዙርያ የማህበራዊ ሚድያ ድርጅቶች ለበርካቶች ዋነኛ የዜና ማግኛ ዘዴ ከሆኑ ሰነባብተዋል። እንደውም እንደ ኢትዮጵያ ባሉ በማደግ ላይ ባሉ ሀገራት ውስጥ የሚገኙ ዜጎች ጋዜጣ ከመግዛት ይልቅ በስልካቸው ዜና ማግኘት ይቀላቸዋል፣ ቴሌቭዥን እና ሬድዮ ከመመልከት እና ከመስማት ይልቅ ፌስቡክን ወይም ቴሌግራምን በቀላሉ መጠቀምን ይመርጣሉ። 

ይህ ወደ ማህበራዊ ሚድያ በፍጥነት የሚደረገውን ጉዞ ተከትሎ ሁሉም ሊባል በሚችል ደረጃ የዜና ተቋማትም ዜናዎቻቸውን እዚያው ላይ ያቀርባሉ፣ ግለሰቦች እና ሌሎች ድርጅቶችም መረጃዎችን እና ሀሳቦችን በስፋት ያንሸራሽራሉ።  

የመረጃ ፍሰቱ ወደ ማህበራዊ ሚድያ ድርጅቶች ማጋደሉ በራሱ ችግር ባይሆንም ይህን ተከትሎ አንዳንድ አካላት ሀሰተኛ መረጃዎችን እና የጥላቻ ንግግሮችን በቀላሉ እንዲያስተላልፉ በር ከፍቷል። ይህም በራሱ ቀውሶችን ፈጥሯል ማለት ባይቻል እንኳ የተከሰቱ ችግሮችን በማባባስ ከፍተኛ አስተዋፅኦ አድርጓል፣ እያደረገም ይገኛል። 

ታድያ ብዙዎች በዚህ ወቅት የሚጠይቁት “የማህበራዊ ሚድያ ድርጅቶች ምን እየሰሩ ነው?” የሚል ጥያቄን ነው። 

እንደ ፌስቡክ ያሉ በየአመቱ በቢልዮን ዶላር የሚገመት ትርፍን የሚያጋብሱ የማህበራዊ ሚድያ ድርጅቶች ገፆቻቸውን ለሁሉም ተስማሚ እና ጉዳት-አልባ ማድረግ እንዳልቻሉ ብዙ ሪፖርቶች ይጠቁማሉ። ለምሳሌ ባሳለፍነው ሳምንት ይህን የድርጅቶቹን ቸልተኝነት በመቃወም የእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ ቡድኖች የማህበራዊ ሚድያ ገፆች ላይ አድማ መተዋል። 

የማህበራዊ ሚድያ ድርጅቶች አደገኛ ንግግሮችን፣ ግጭት ቀስቃሽ ፅሁፎችን እንዲሁም ጥላቻን የሚሰብኩ ድርጊቶችን እየተከታተሉ እርምጃ ሊወስዱ እንደሚገባ ግልፅ ነው። በአዲሱ የኢትዮጵያ የሀሰተኛ እና የጥላቻ ንግግር መከላከያ አዋጅ ላይም ይህ በግልፅ ተቀምጧል። 

እርግጥ ነው ፌስቡክ በቅርቡ አንዳንድ ልጥፎችን እያጋራ ይገኛል፣ አንዳንድ ቢልቦርዶችን ጭምር በመጠቀም መልእክት እያስተላለፈ እንዳለም ተመልክተናል። ከዚህ በተጨማሪ ግን በሀገር ውስጥ ያለውን ጉዳይ በቅጡ የሚረዱ እና ትንታኔ መስጠት የሚችሉ ሰዎችን በማሰባሰብ እና በማሰማራት የሀሰተኛ መረጃዎች እና የጥላቻ ንግግሮች ሲገኙ አስቸኳይ እርምጃ ሊወስድ ይገባል። 

ይህን አለማድረግ ሀላፊነትን አለመወጣት ብቻ ሳይሆን የህግ ተጠያቂነትንም ሊያስከትል የሚችል ጉዳይ ነው።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::