የማህበራዊ ሚዲያ ድርጅቶች ያልተገቡ ይዘቶችን የመቆጣጠር ድርሻ እና ሀላፊነት!

ሰዎች የማህበራዊ ትስስር ሚዲያዎችን መጠቀማቸው እየበዛ በመጣ ቁጥር በዛው ልክ የሀሰተኛ መረጃዎችን የያዙ ጽሁፎችም እየተበራከቱ እየመጡ ነው። ማንም ሰው አካውንት ከፍቶ በሚፈልገው አርእስት ዙሪያ የሚፈልገውን መጻፍ ይችላል። መረጃው ሀሰት ከመሆኑ በላይ የሚያሳስበው እንደዚህ አይነት መረጃዎች የመዛባት እና የመሰራጨት እድላቸው ከፍተኛ መሆኑ ነው።

በባለፉት ሶስት አስርት አመታት ውስጥ ሶስት በጣም ሰፋፊ እና የተለያዩ የሀሰተኛ መረጃ ምድቦች ተፈጥረዋል። አንደኛው ሃያላን መንግስታት ማህበራዊ ሚዲያ ላይ በሚናፈስ የሀሰተኛ መረጃ በሌሎች ሃገራት ላይ ባልሆነ መንገድ መጠቅም ነው። ለምሳሌ ያህል ሩሲያ በአሜሪካ ምርጫ ላይ ያደረገችውን ጣልቃገብነት ማየት እንችላለን። በሁለተኛነት ደረጃ ደግሞ አንዳንድ አምባገነን መንግስታት በሃገራቸው ያሉ የተቃዋሚ አካላትን ለማጥቃት የሚጠቀሙበት ነው። የማይናማር መንግስት በሮሂንግያ ሙስሊሞች ላይ የፈጸመውን ጥቃት እንደ ምሳሌነት መጥቀስ ይቻላል። በመጨረሻ ደግሞ የፖለቲካ ፓርቲዎች በሌሎች ተቃዋሚ ፓርቲዎች ላይ የሚነዙት የሀሰተኛ መረጃ እና ፕሮፖጋንዳ ነው።

የማህበራዊ ሚዲያ ድርጅቶች ባለቤቶች እነዚህን እና መሰል በሚዲያዎቻቸውን የሚወጡ ጉዳዮችን እየተመለከቱም ቢሆን እዚህ ግባ የሚባል ነገር ለመለወጥ ሲሰሩ አይታዩም።

በተለይ በምርጫ ወቅት በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ የሚወጡ መረጃዎች በይበልጥ አደገኛ ናቸው። ለዚህም ነው ማህበራዊ ሚዲያዎች በተለይ በዚህ ወቅት ላይ የሰዎችን የመናገርን መብት በማገድ እና በገጾቻቸው ላይ የሚዛቡትን መረጃዎች በመቆጣጠር መካከል ሚዛኑን መጠበቅ ያለባቸው።

ለምሳሌ በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ትዊተር እየወሰደ ያለው የመቆጣጠር ዘዴን አንዳንዶች እንደ ጥሩ እርምጃ ይወስዱታል። አንድ መረጃ ሃሰተኛ ወይም የተዛባ ነገር በውስጡ እንዳለው ከታመነ ከታቹ ስለ ጽሁፉ ፋክት ቼክ የተደረገ መረጃን ያስቀምጣሉ።
ፌስቡክ እና ትዊተር አንዳንዴ በሚዲያዎቻቸው ላይ የሚወጡት አጸያፊ የቃላት ይዘት ያላቸው ከሆኑ ያንን ጽሁፍ ፈልጎ አግኝቶ ለማውረድ ሲሞክሩ ይታያል፣ ይህን ያደርጋሉ ማለት ግን ፖለቲካዊ ይዘት ያላቸውን ጽሁፎች ለመቆጣጠር ይሞክራሉ/ይፈልጋሉ ማለት አይደለም፣ ለእነዚህ ድርጅቶች ይህንን ማድረግ ብዙ ወጪ እና ድካም ይሆናል።

ለእነዚህ ትልልቅ ድርጅቶች የተለያዩ መንግስታት በየሚዲያዎቻቸው ላይ የሚወጡትን መረጃዎች እንዲቆጣጠሩ ቢጠይቁም እዚህ ግባ የሚባል መልስ ሲሰጡ አልታዩም። ለዚህም ነው እንደ አውስትራሊያ እና ሲንጋፖር የመሳሰሉት ሃገራት ለማህበራዊ ሚዲያ ተቋማት ህግጋትን ያወጡት፣ ለማህበራዊ ሚዲያ ተቋማት ህግ ካወጡ ሃገሮች ውስጥ ኢትዮጵያ አንዷ ናት።

የጥላቻ ንግግርና የሐሰተኛ መረጃ ስርጭትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በወጣው አዋጅ ላይ ለተቋማትና አገልግሎት ሰጪዎች ከተሰጠው ኃላፊነት ላይ “ 1/ ማንኛውም የማህበራዊ ሚዲያ አገልግሎት የሚሰጥ ድርጅት የጥላቻ ንግግርና የሐሰተኛ መረጃ ስርጭትን ለመቆጣጠርና ለመግታት ጥረት ማድረግ አለበት።” ይላል። “2/ ድርጅቱ የጥላቻ ንግግርን ወይም የሐሰተኛ መረጃ ስርጭትን የተመለከተ ጥቆማ ሲደርሰው በሀያ አራት ሰዓት ውስጥ ይህን መሰል መልዕክቶችን ወይም ንግግሮችን ከአግልግሎት አውታሩ ሊያስወግድ ይገባል” ይላል።

በተጨማሪም ደግሞ የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን የማህበራዊ ሚዲያ አገልግሎት የሚሰጡ ድርጅቶች የተቀመጠባቸውን ግዴታ በአግባቡ መወጣታቸውን መከታተል እንዳለበት ህጉ ይጠቅሳል።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::