ስለ ማህበራዊ ሚዲያ መለያ ጠለፋዎች

ባሳለፍነው ሳምንት የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽንና የኢትዮጵያ አየር መንገድ የፌስቡክ ገጾች ከቁጥጥር ውጭ ወጥተው እንደነበር ይታወሳል። ገጾቹ ከቁጥጥር ውጭ ሆነው በቆዩባቸው ጊዜያት የድርጅቶቹን አቋም የማያንጸባርቁ መልዕክቶች ስለመተላለፋቸውም በተቋማቱ ተገልጿል። 

ምንም እንኳን ገጾቹ እንዴትና በማን እንደተጠለፉ እስካሁን ባይነገርም ክስተቱ ስለ ሳይበር ደህንነት በተለይም ስለይለፍ ቃላቶች (passwords) ቆም ብለን እንድናስብ የሚያሳስቡ ነበሩ። 

ኢትዮጵያ ቼክም የባለፈው ሳምንት ክስተቶችን እንደገፊ ምክንያት በመጠቀም ተቋማትና ግለሰቦች የማህበራዊ ሚዲያ፣ የኢሜል፣ የድረ-ገጽ እንዲሁም የሌሎችን አካውንቶች ደህንነት ለማጠናከር ይረዳሉ ያላቸው መሰረታዊ የሳይበር ደህንነት መጠበቂያ ዘዴዎችን በዛሬው የሰኞ መልዕክት አቅርቧል። 

የአካዎንቶችዎን ደህንነት ለመጠበቅ ከሚረዱ ስልቶች መካከል ለተያዩ አካውንቶች ተመሳሳይ የይለፍ ቃል አለመጠቀም አንዱ ነው። ለተለያየ አገልግሎት ለሚጠቀሙባቸው አካውንቶች ተመሳሳይ የይለፍ ቃል መጠቀም የይለፍ ቃሉ እንዳጋጣሚ በፈልቃቂዎች ቁጥጥር ስር ቢገባ ሁሉንም አካውንቶች ለአደጋ ያጋልጣል። 

ስለሆነም ለየአንዳንዱ አካውንትዎት የተለያየና ጠንካራ የይለፍ ቃል ይጠቀሙ። ለዚህ ደግሞ የይለፍ ቃል የሚያስተናብሩ መገልገያዎችን (password managers) ይረዱዎታል። መገልገያዎቹ የይለፍ ቃላቶችን በቀላሉ እንዲያስታውሱ ከማገዝ በተጨማሪ ጠንካራ የይለፍ ቃል በመምረጥም የረዱዎታል። 

ባለሁለት ደርዝ ማረጋገጫ (two-factor authentication) መጠቀም ሌላኛው የአካውንትዎን ደህንነት ለማጠናከር ከሚያግዙ ዘዴዎች መካከል የሚጠቀስ ነው። ባለሁለት ደርዝ ማረጋገጫ ወደ አካውንትዎ ለማለፍ ከመጠቀሚያ ስምዎና ከይለፍ ቃልዎ በተጨማሪ ሌላ ማረጋገጫ በመጠየቅ የአካውንትዎን ደህንነት ይበልጥ ከፍ ያደርገዋል። ጂሜል፣ ድሮፕቦክስ (Dropbox)፣ አውትሉክ (Outlook) እና ሌሎች የባለሁለት ደርዝ ማረጋገጫ አገልግሎት ከሚሰጡ መተግበሪያዎች መካከል ይጠቀሳሉ። 

በተጨማሪም አጠራጣሪ የሆኑ ማስፈንጠሪያዎችን (links) አለመከተል፣ በኢንተርኔት ማሰሻዎች (browsers) የይለፍ ቃሎችን ሴቭ አለማድረግ እንዲሁም በፐብሊክ ቦታዎች የዋይፍይ አገልግሎት ካለጥንቃቄ አለመጠቀም የአካውንትዎን ደህንነት ለመጠበቅ ይረዳሉ። በስልክዎ ላይ የሚገኙ ፓስኮዶችን (passcodes) በአግባቡ መጠቀምም የአካውንትዎን ደህንነት ለመጠበቅ በእጅጉ ይረዳል። 

ፓስኮዶችን ሲጠቀሙ ከተለመደው አራት ዲጅት ይልቅ እንደ አሻራ ያሉ የባዮሜትሪክ ማለፊያዎች መጠቀም ይምረጡ። ፀረ-ቫይረሶችን (anti-virus) አዘውትሮ መጠቀም እንዲሁም በስልክዎትና በኮምፒተርዎት የሚገኙ መገልገያዎችን በየጊዜው አፕዴት ማድረግም የአካውንትዎን ደህንነት ለማረጋገጥ ይረዳሉ።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::