የጤና ሚኒስቴር ከዛሬ የካቲት 7/2014 ዓ.ም ጀምሮ ሁለተኛ ዙር የኮቪድ-19 ክትባት በዘመቻ መልክ እንደሚሰጥ አስታውቋል!

ለዚህም ከ20 ሚሊዮን በላይ ክትባቶች ለሁሉም ክልሎች መላኩንና ባለሙያዎችም ሰልጥነው መሰማራታቸውን ገልጿል። በዚህኛው ዙር የክትባት ዘመቻ ክትባት ካልወሰዱና የመጀመሪያውን ወስደው ሁለተኛውን ካልተከተቡ ሰዎች በተጨማሪ የማጠናከሪያ ክትባት (Booster Dose) የሚያስፈልጋቸው ክትባቱን መውሰድ እንደሚችሉ ተገልጿል።

የማጠናከሪያ ክትባት ከዚህ በፊት የተሟላ የኮቪድ-19 ክትባት ከተወሰደና የመከላከል አቅም ከተገነባ በኃላ በጊዜ ሂደት የሚከሰተው መሸርሸር እንደገና ለማበርታት የሚሰጥ ተጨማሪ ከትባት ነው። በነሐሴ ወር በአሜሪካ የበሽታዎች መከላከያና መቆጣጣሪያ ድርጅት (US-CDC) ድረ-ገጽ ለንባብ የበቃና የኒዮርክ ከተማ ነዋሪዎችን የቃኘ የጥናት ውጤት የኮቪድ- ክትባት ውጤታማነት በሶስት ወራት ውስጥ ከ92% ወደ 80% ዝቅ እንደሚል አሳይቷል።

ይህም ማለት የማጠናከሪያ ክትባቱ የመጀመሪያውን ዙር ክትባት ከወሰዱ በኃላ በጊዜ ሂደት የሚከሰትን የመከላከል አቅም መቀነስ በማጎልበት በኮቪድ-19 የመያዝ ዕድላችንን እንዲሁም በበሽታው ምክንያት የሚመጣን ስቃይ ይቀንሳል ማለት ነው።

ለምሳሌ እ.አ.አ ጥር 22/2022 ዓ.ም በአሜሪካ የህክምና ማህበር የምርምር መጽሔት (Journal of American Medica Association) ለንባብ የበቃ የጥናት ውጤት የተሟላ የመጀመሪያ ዙር ክትባት ወስደው ከወራት በኃላ የማጠናከሪያ ክትባት የወሰዱ ሰዎች የተሻለ የመከላከል ብቃት እንዲሁም በበሽታው ምክንያት የሚከሰትን ስቃይና ሞትን የመቀነስ ዕድላቸው የተሻለ መሆኑን አመላክቷል። ሌሎች የጥናት ውጤቶችም ተመሳሳይነት ያለው ግኝት ማሳየታቸውን ተመልክተናል።

ስለሆነም የኮቪድ-19 ማጠናከሪያ ክትባት የሚያስፈልግዎ ከሆነ ወደ ጤና ተቋማት በመሄድ የህክምና ባለሙያዎችን ያማክሩ፤ ይከተቡ።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::