ኢትዮጵያ ቼክ የመረጃ ማንጠር ስራ በይፋ ከጀመረ አንድ አመት አለፈው፣ ጉዞው ምን ይመስል ነበር?

በጣም በጥቂት የሰው ኃይል ስራውን የጀመረው ኢትዮጵያ ቼክ በዚህ ጊዜ ውስጥ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሀሠተኛና የተዛቡ መረጃዎችን አንጥሯል፣ በርካታ ተመሳስለው የተከፈቱ ሀሠተኛ የማህበራዊ ሚዲያ ገጾችንና አካውንቶችን አጋልጧል፣ በስፋት የተሰራጩ አሉባልታዎችን ምንጫቸውን በመከተል አርቋል (rumour tracking)፣ የሚዲያ ንቃትን የሚያጎለብቱ ጽሁፎችን አጋርቷል፣ እንዲሁም መረጃ ማንጠርን የተመለከቱ ስልጠናዎችን ወደ 70 ለሚጠጉ ጋዜጠኞች ሰጥቷል። 

ስራዎቻችን በማህበራዊ ሚድያ ገፆቻችን እንዲሁም በድረ-ገፃችን አማካኝነት በአጠቃላይ ወደ 6 ሚልዮን ገደማ ለሚሆኑ ሰዎች መድረስ ችለዋል። በሰራናቸው ስራዎች ሁሉ እውነታን መያዝ እና ገለልተኝነት የተከተልናቸው መርሆች ናቸው። 

ይህም ሆኖ ጉዟችን አልጋ ባልጋ ነበር ማለት አይቻልም። መረጃ የማግኘት ችግር፣ የቴክኖሎጂ ውስንነት፣ የሀሠተኛ መረጃዎች ባህሪ እየተወሳሰበ መምጣት ወዘተ ካጋጠሙን ተግዳሮቶች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው። በተለይም የተከሰቱና በመከሰት ላይ ያሉ ግጭቶችና ባህሪያቸው መረጃ በማንጠር ስራ ላይ አዳዲስ ተግዳሮቶችን ይዘው ብቅ ማለታቸው አልቀረም። 

በግጭት ወቅት መረጃ ለማንጠር ተግዳሮት ከሚሆኑ ማነቆዎች መካከል ማመሳከሪያ መረጃ ማግኘት አንዱ ነው። በተለይም ወታደራዊና የውጭ ጉዳይን የተመለከቱ መረጃዎች ሚስጥራዊ (classified) ከመሆናቸው አኳያ መረጃ የማንጠር ስራን ያከብዱታል። እንደዚህ ያሉ መረጃዎች ለህዝብ፣ ለጋዜጠኞች፣ ለተመራማሪዎች ወዘተ ይፋ የሚሆኑት (declassified) ከረጅም ጊዜያት በኃላ መሆኑ ይታወቃል። 

የግጭት ቀጠና በሆኑ አካባቢዎች ተከስተዋል ተብለው የሚሰራጩ መረጃዎችን ለማጣራት ማነቆ ከሚሆኑ ጉዳዮች ሌላኛው በአካባቢዎቹ የስልክና የኢንተርኔት አገልግሎት መቋረጥ ነው። ይህም ማመሳከሪያ መረጃዎችን ከምንጩ በማግኘት እውነትን ከሀሠት ለመለየት በሚደረገው መረጃ የማንጠር ሂደት በእንቅፋትነት ይጠቀሳል። 

ከዚህ በተጨማሪም የቴክኖሎጅ ውስንነት በግጭት ቀጠናዎች የተወሰዱ ናቸው ተብለው የሚሰራጩ ፎቶዎችንና ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማንጠር የሚገጥም ሌላኛው ተግዳሮት ነው። ለምሳሌ ከግጭት ቀጠናዎች ተወስደዋል ተብለው የሚሰራጩ ፎቶዎችንና ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ትክክለኝነት ለመለየት (geolocate) የሚግዙ አሁናዊ (latest) የሳተላይት ምስሎችን ማግኘት እንደ አንድ ተግዳሮት ሊወሰድ ይችላል። 

በግጭት ወቅት ከሀሠተኛና የተዛቡ መረጃዎች ጋር መሳለመሳ የሚሰራጨው ፕሮፓጋንዳ ሌላኛው መረጃ የማንጠር ስራ ከሚያከብዱ ጉዳዮች መካከል ሊጠቀስ ይችላል። ፕሮፓጋንዳ ለዘመናት ግጭት በተፈጠረበት ወቅትና ቦታ ሁሉ አብሮ ብቅ የሚል የመረጃ አይነት መሆኑ እሙን ነው። ከሀሠተኛ መረጃ የሚለዩትም የራሱ ባህሪያት እንዳሉት የሚታወቅ ነው። ነገር ግን በሁሉም ወገን የተሰለፉ የፕሮፓጋንዳ አመንጭዎች በአብዛኛው ዋነኛ የመረጃ ምንጭ የመሆናቸው አግባብ መረጃ የማንጠርን ስራ የከበደ ያደርገዋል። 

ከላይ የተገለጹትና ሌሎች ተግዳሮቶች ቢኖሩም ኢትዮጵያ ቼክ በተቻለው አቅም ዜጎች ሃቀኛ መረጃ እንዲያገኙ እንዲሁም የሚዲያ ንቃታቸውን እንዲያጎለብቱ በዚህም በእውነትና በዕውቀት ላይ የተመሰረተ ውሳኔ እንዲወስኑ የሚያደርገውን ጥረት አጠናክሮ ይቀጥላል። 

ተከታዮቻችንም በማህበራዊ ሚዲያ እንዲሁም በሌሉች የተግባቦት ዘዴዎች የሚደርሳቸውን መረጃ ከመቀበላቸውና ከማጋራታቸው በፊት ቆም ብለው እንዲያጤኑ እንመክራለን። የሀሠተኛና የተዛባ መረጃ ስርጭትን ለመግታት የበኩልዎን ይወጡ።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::