ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት ድንበር የት ድረስ መሆን ይገባዋል?

twitter verification

ሐምሌ 24፣ 2015

ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት አዎንታዊ ሚናው የጎላ መሆኑ ታምኖበት በርከት ባሉ ዓለም አቀፍ ድንጋጌዎች እና ስምምነቶች እንዲሁም የሀገራት ህገመንግስቶች በግለጽ የሰፈረ መርህ መሆኑ እውነት ነው። የሰዎች ሀሳባቸውን በነጻነት መግለጽ ዲሞክራሲያዊ ስርዐትን ያጎለብታል፣ ተጠያቂነትንና ግልጸኝነትን ያሰፍናል፣ ፈጠራንና ዘርፈ ብዙ እድገትን ያረጋግጣል፣ መተማመንና ሰላምን ያሰፍናል።

ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት አዎንታዊ ሚናው በግልጽ የሚታወቅ ቢሆንም “ድንበሩ የት ድረስ ነው?” የሚለው ጥያቄ ለበርካታ ዓመታት አካዳሚያዊና ፖለቲካዊ ውዝግ ሲፈጥር መቆየቱ እሙን ነው። ይህን በተመለከተም በርካታ መጽሃፍት ተጽፈዋል፤ የአደባባያ ሙግቶች ተደምጠዋል፤ የምርምር ወረቀቶች ተሰንደዋል።

በተለይም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ከኢንተርኔትና ከማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች መስፋፋት ጋር ተያይዞ የሀሠተኛና የተዛቡ መረጃዎች፣ የሴራ ትንተናዎች እንዲሁም የጥላቻ መልዕክቶች መበራከት ጥያቄው እንዲያገረሽ አድርገውታል።

ድንበሩን ማስመር ያልተፈታ ቋጠሮ መሆኑን የሚከራከሩ ወገኖች አሁንም ያሉ ቢሆንም የሀሠተኛና የተዛቡ መረጃዎች፣ የሴራ ትንተናዎች እንዲሁም የጥላቻ መልዕክቶች እያደረሱት ካሉት ከበድ ያለ ጉዳት አኳያ ለከት ሊበጅለት ይገባል ድንበርም አለው የሚሉ ድምጾች ጎላ ብለው መሰማት ጀምረዋል። እነዚህ አካላት አሉታዊ ይዘቶችን በግልጽ መበየን ይቻላል የሚል መከራከሪያም ያቀርባሉ።

ይሁንና ይህን በጎ ድምጽ እንደመከራከሪያነት በመጠቀም የሀሳብን በነጻነት የመግለጽ ልዕልናን ለመደፍጠጥ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ይስተዋላሉ። በምሳሌነትም ሀሠተኛና የተዛቡ መረጃዎችን ጨምሮ የአሉታዊ መመልዕክቶችን ጉዳት ለመከላከል በሚል ምክንያት የሚወጡ አፋኝ ህጎችን መጥቀስ ይቻላል።

በአንጻሩ ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት አክራሪዎች በሚጋሯቸው አሉታዊ ይዘቶች አንጻር የሚቀርብባቸውን ወቀሳና ክስ ለመሞገት ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት ድንበር-የለሽነትን በመከራከሪያነት ያነሳሉ።

እንዲህ ያለው የሀሳብ በነጻነት መግለጽ መብትን ድንበር እንደፈለጉ የማጥበብ እና የማስፋት እንቅስቃሴ ችግሮችን የማስቀጠል እድሉ ሰፊ መሆኑን ብዙዎች ይስማሙበታል።

ስለሆነም የሀሠተኛና የተዛቡ መረጃዎች፣ የሴራ ትንተናዎች እንዲሁም የጥላቻ መልዕክቶችን ጉዳት ለማረቅ ድንበሩን እንደፈለጉ ማጥበብ እና ማስፋት ሳይሆን ድንበሩን በትክክል እና በምክንያታዊነት ማስመር እንዲሁም አሉታዊ ይዘቶችን በሚገባ መበየን ተፈላጊውን ውጤት ለማምጣት ቀዳሚ ተግባር መሆኑ ሊታመንበት ይገባል እንላለን።

በተመሳሳይም ለከት የለሽ ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ መበት ከበድ ያለ ጉዳት እንደሚያደርስ በማመን ቆም ብለን ማሰተዋልና ድንበር ማስመር ተገቢ ነው እንላለን።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::