የማህበራዊ ሚዲያ ገጾች እና አካውንቶችን እንዴት ቬሪፋይ ማስደረግ ይቻላል?

ሐምሌ 18/2014

የማህበራዊ ሚዲያ ማረጋገጫ (verification) ለመጀመሪያ ጊዜ ይፋ ሲደረግ ለታዋቂ ግለሰቦች እና ድርጅቶች እንዲሁም ከፍተኛ ተከታዮች ላሏቸው ሰዎች ብቻ ተጠብቆ ነበር። ከጊዜ በኋላ ግን በርከት ያሉ ኩባንያዎችን፣ ጋዜጠኞችን፣ አክቲቪስቶችን፣ የመንግስታት ሀላፊዎችን እና ተጽዕኖ ፈጣሪዎችን ለማካተት ጥረት ተደርጓል፡፡

በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ ይህንን ማረጋገጫ (verification) ማግኘት ብዙ ጥቅሞች አሉት። ከእነዚህም መሀል:

 • ከተከታታዮች ጋር መተማመንን ለመገንባት
 • ማህበራዊ ማስረጃን (social proof) ለማግኘት
 • ተመሳስለው የሚከፈቱ አካውንቶችን፣ ገፆችን እና ቻናሎችን በቀላሉ ለመለየት፣ እንዲሁም
 • የተከታታዮችን እድገት ለማግኘት ወዘተ ሊጠቀሱ ይችላሉ

በትዊተር ላይ ማረጋገጫን (verification) ማግኘት: በትዊተር ላይ ማረጋገጫን ለማግኘት በሚከተሉት ምድቦች ውስጥ መገኘት ያስፈልጋል:

 • የመንግስት አካል
 • የምርት ድርጅቶች፣ ኩባንያዎች እና ለትርፍ ያልተቋቋሙ ድርጅቶች
 • ጋዜጠኞች እና የዜና ድርጅቶች ባልደረባ
 • የስፖርት ድርጅቶች እና ስፖርተኞች
 • መዝናኛ ኢንደስትሪ ውስጥ ያሉ መሆን
 • አክቲቪስቶች፣ ተፅዕኖ ፈጣሪዎች መሆን

የትዊተርን ሰማያዊ ባጅ ለመቀበል ገጹ ትክክለኛ (authentic)፣ ታዋቂ (notable) እና ንቁ (active) መሆን አለበት።

ትክክለኛ(authentic): የትዊተርን ማረጋገጫ ለማግኘት ትዊተር ማንነትዎን ማረጋገጥ ይፈልጋል። ማንነትዎን ለማረጋገጥ ከሶስቱ ዘዴዎች ውስጥ አንዱን መምረጥ ይቻላል። እነሱም: የተረጋገጠ ድረ-ገፅ፣ መታወቂያ ወይም የኢሜል አድራሻን መጠቀም ይቻላል።

ታዋቂ (notable): አካውንቱ ከታወቀ ግለሰብ ወይም ድርጅት ጋር በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ የተያያዘ መሆን አለበት። ይህንንም ትስስር ትዊተር በራሱ ወይም አብረው በሚሰሩ ድርጅቶች ይረጋገጣል።

ንቁ (active): የትዊተር አካውንቱ የትዊተር ህጎችን ባከበረ መልኩ ንቁ መሆን አለበት። ይኼ ማለት የመገለጫ ስም እና የመገለጫ ምስል ሊኖረው ይገባል። ንቁ አጠቃቀም ማለት ባለፉት 6 ወራት ውስጥ አካውንቱን መጠቀም አለብዎት። ከዚህም በተጨማሪ አካውንቱ የተረጋገጠ የኢሜል አድራሻ ወይም የስልክ ቁጥር ሊኖረው ይገባል።

አንዴ የትዊተር ማረጋገጫ ከተሰጠ በኋላ የተጠቃሚ ስምዎን (username) ከቀየሩ፣ አካውንቱ እንቅስቃሴ አልባ ከሆነ፣ ወይም መጀመሪያ መረጋገጫው በተሰጠበት ቦታ ላይ ካልሆኑ የተሰጠው ማረጋገጫ ሊወርድ ይችላል። Note: ትዊተር ከቀናት በፊት የማረጋገጫ ጥያቄዎችን ለግዜው መቀበል እንዳቆመ አስታውቋል።

በፌስቡክ እንዴት ማረጋገጫ ይሰጣል?

 • በመጀመርያ ወደ ፌስቡክ ሰማያዊ ማረጋገጫ ባጅ መጠየቂያ ገጽ (Blue Verification Badge Page) ይሂዱ (ሊንክ)።
 • የማረጋገጫ ዓይነትዎን (ገጽ ወይም አካውንት) ይምረጡ
 • ምድብ ይምረጡ፣ አገርዎን ይምረጡ፣ መታወቂያ ያስቀምጡ፣ የእርስዎ መለያ/አካውንት ለምን መረጋገጥ እንዳለበት ያብራሩ፣ ከዛም ‘ላክ’ የሚለውን ይጫኑ።

ለግለሰቦች የመንጃ ፈቃድ ወይም ሌላ በመንግስት የተሰጠ የመታወቂያ ካርድ ይበቃል። ለንግድ ገጽ ደግሞ የምስረታ የምስክር ወረቀትን፣ የኩባንያዎን ስልክ ወይም የፍጆታ ሂሳብ ወይም የግብር ሰነዶችን ማቅረብ ይችላሉ። ጥያቄዎን ከላኩ በኋላ የፌስቡክ ማረጋገጫ ቡድን መረጃዎን ይገመግምና እና ውሳኔ ይሰጣል።

ፌስቡክ ጥያቄውን ከተቀበለው በአካውንቱ ላይ ሰማያዊ ባጅ ይታያል። ሆኖም ጥያቄዎ ውድቅ ከተደረገ ከ30 ቀናት በኋላ እንደገና ማመልከት ይችላሉ። የፌስቡክ ማረጋገጫ የብቁነት መስፈርቶች ከኢንስታግራም (Instagram) ጋር ተመሳሳይ ናቸው።

እንዲሁ በዩትዩብ (YouTube) ላይ ማረጋገጫ ማግኘት ይቻላል። የዩትዩብ ቻናሉ ለማረጋገጫ ባጅ ብቁ ከሆነ ግራጫ አመልካች ምልክቱን ለማግኘት በማረጋገጫ ባጅ ገጹ ላይ ማመልከት ይችላሉ።

ዩትዩብ መስፈርቶቹን የሚያሟላ መሆኑን ለማየት ቻናሉን ይገመግማል። የማረጋገጫ ባጅ ለመቀበል የዩትዩብ ቻናሉ ቢያንስ 100,000 ተመዝጋቢዎች ሊኖረው እና መስፈርቶችን ማሟላት አለበት።

ማስታወሻ: ሁሉም የማህበራዊ ሚድያ ድርጅቶች ማረጋገጫ ለመስጠት ገንዘብ አያስከፍሉም፣ ስለዚህ “ማረጋገጫ እንዲሰጥዎት እናደርጋለን” ብለው ገንዘብ ከሚጠይቁ ግለሰቦች እና ድርጅቶች ራስዎን ይጠብቁ።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

  ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::