በአዲስ ዓመት እንደ አዲስ እንጀምር!

ውሸት ስለራሳችንም ይሁን ስላለንበት ሁኔታ የተዛባ እና የተሳሳተ ግንዛቤን ይፈጥራል። በተፈጥሮው ሚዛኑን የሳተና የተንሻፈፈ እይታን መፍጠር ዋነኛ፣ ምናልባትም ብቸኛው ግቡ ነው። በዚህ በተሳሳተ ወይም በተዛባ ግንዛቤ ላይ ተመስርቶ የሚወሰድ ማንኛውም አቋም ወይም ውሳኔ ደግሞ መሬት ላይ ካለው ሀቅ ጋር የተጣላ፣ ውጤቱም ዘላቂነት የሌለው ይሆናል።  

ባለፈው ዓመት ከተሰሩ ጥናቶች ውስጥ የአውሮፓ ህብረት የሰላም ኢንስቲትዩት በዓመቱ አጋማሽ አካባቢ “Fake News Misinformation and Hate Speech in Ethiopia: A Vulnerability Assessment” በሚል ርዕስ ይፋ ያደረገው ጽሑፍ እንደታዘበው ጥናቱ በተደረገበት የ6 ወር ጊዜ ውስጥ የተወሰዱ ናሙናዎች እንደሚያሳዩት የሚበዙት ሀሰተኛ እና አሳሳች መረጃዎች እንዲሁም የጥላቻ ንግግሮች በጣም ውስን በሆኑ ርዕሶች ላይ ትኩረት ያደረጉ ናቸው። 

እነዚህ ርዕሶች ብሔርን፣ ሀይማኖትን፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ስርዓትን፣ የህዳሴ ግድቡን፣ ኮቪድ-19ን እንዲሁም ዓለም አቀፍ ግንኙነትን የተመለከቱ እንደነበሩ ይህ ጥናት ያመለክታል። እነዚህ ርዕሶች እያንዳንዱን ኢትዮጵያዊ የሚመለከቱ፣ ህይወቱን በአንድ ወይም በሌላ መልኩ የሚነኩ ከሁሉም በላይ ግን ስሜትን የመኮርኮር አቅማቸው ከፍተኛ የሆኑ መሆናቸው አሳሳቢ ያደርገዋል።

ለዚህ ነው ሀሰተኛ መረጃን የመዋጋት ስራ እያንዳንዱ የሕብረተሰብ ክፍል ጊዜ እና ቦታ ሳይወስነው ጉዳዬ ብሎ ሊይዘው ይገባል የምንለው። ባለፈው ሳምንት በሸኘነው አሮጌው አመትም ሊፈቱ የሚችሉ (እና የሚገቡ) ልዩነቶች በሀሰተኛ እና በአሳሳች መረጃዎች ምክንያት ያለልክ እንዲለጠጡ እና እንዲገዝፉ መሆናቸውን አስተውለናል።

ነገር ግን አሁን አዲስ ምዕራፍ ጀምረናል። የጊዜ አዲስ ምዕራፍ። ካለፈው አመት ተጎትተው የመጡት ሀገራዊ ጉዳዮች በቦታቸው እንዳሉ ቢሆኑም፣ ይህ አዲስ ጊዜ አዲስ ውጤት እንዲያመጣ ከቀደመው ጊዜ መማር ያስፈልጋል። ሀሰተኛ እና አሳሳች መረጃን ብቻ በመዋጋት ምትክ የሌለው ውጤት እና ለውጥ ማምጣት ይቻላል ብሎ ኢትዮጵያ ቼክ በፅኑ ያምናል። 

አሁን የጀመርነው አዲስ ዓመትም ከኋላ ትተነው ከመጣነው የተነጠለ፣ የተሻለ ለማድረግ ሀሰተኛ እና አሳሳች መረጃ ላይ እንዝመት። ሀሰተኛ እና አሳሳች መረጃዎችን ባለመፍጠር፣ ባለማጋራት እንዲሁም በማጋለጥ እንረባረብ። 

መልካም ሰኞ! መልካም ዓመት!

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::