የምርጫ ውጤት ትንበያ ችግሮቹ እና በህግ የተቀመጡ ክልከላዎች!

የዳበረ የዴሞክራሲ ስርዐት ባለባቸው ሀገራት የምርጫ ዝንባሌ መለኪያዎችን (polls) መጠቀም በጣም የተለመደ ሲሆን ጠቅላላ ሂደቱም በትላልቅ የትምህርትና የምርምር ተቋማት፣ በስታስቲክስና መርጃ ድርጅቶች እንዲሁም በሚዲያ ተቋማት ይከወናል። የዝንባሌ መለኪያዎቹ ቀደም ባሉት አመታት በስልክና በፖስታ ከቅርብ አመታት ወዲህ በአብዛኛው በኢንተርኔት ይሰራሉ።

በርከት ያሉ የማህበራዊ ሳይንስ የጥናት ውጤቶች እንደሚያሳዩት የምርጫ ዝንባሌ መለኪያ ውጤቶች የመራጮች ውሳኔ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ያሳድራሉ።

በኢትዮጵያም የስድስተኛው አገር አቀፍ ምርጫ ድምጽ መስጫ ቀን መቃረቡን ተከትሎ የምርጫ ዝንባሌ መለኪያዎች በተለይም በቴሌግራምና በትዊተር ገጾች ሲለጠፉና ውጤታቸውም ይፋ ሲደረግ ተመልክተናል።

የምርጫ ዝንባሌ መለኪያዎቹ በአብዛኛው በርከት ያለ ተከታይ ባላቸው ግለሰቦች፣ አክቲቪስቶች፣ ፖለቲከኞች እንዲሁም መረጃ አቅራቢ ገጾች የተዘጋጁ ሲሆን “በመጭው አገር አቀፍ ምርጫ የትኛው ፓርቲ ያሸንፋል?” እንዲሁም “በመጭው ምርጫ በአዲስ አበባ ከተማ ማን ያሸንፋል?” የሚሉት ጥያቄዎች ተደጋግመው የተነሱ ናቸው።

እነዚህ የምርጫ ዝንባሌ መለኪያዎች ዜጎች በምርጫ እንዲሳተፉ የማነቃቃት በጎ ተጽዕኖ ቢኖራቸውም የሚያቀርቡት የዝንባሌ ውጤት ሁልጊዜ ትክክለኛ ነው ማለት አይደለም። አንድ የዝንባሌ መለኪያ በአንጻራዊነት ትክክለኛ ውጤት ለማሳየት ሳይንሳዊ ዘዴን መጠቀም ይጠበቅበታል። ሳይንሳዊ ዘዴ ስንል የጥያቄዎች አዘገጃጀትን፣ የተሳታፊዎች ወካይነትን ወዘተ ያካትታል።

ለምሳሌ በአንድ በኢትዮጵያ ጉዳዮች ላይ በሚያተኩር የትዊተር ገጽ የተሰራና ሶስት ሺህ ገደማ ሰዎች የተሳተፉበት የምርጫ ዝንባሌ መለኪያ ውጤት ሙሉ ለሙሉ ወካይ ነው ለማለት አይቻለም። በውጤቱ ከመስማማታቸን በፊት ‘መጠየቁን የጠየቀው የትዊተር ገጽ ተከታዮች እነማናቸው?’፣ ‘ገጹ ምን አይነት የፖለቲካ ዝንባሌ ያራምዳል?’፣ ‘ተሳታፊዎቹ በምርጫ ለመሳተፍ ብቁ ናቸው (ዕድሜ፣ ዜግነት)?’ ወዘተ የሚሉ ጥያቄዎችን ማንሳት ያስፈልጋል ምክንያቱም እነዚህና መሰል ጉዳዮች የዝንባሌ መለኪያ ውጤት ላይ ተጽዕኗቸው የጎላ ስለሆነ ነው።

በተጨማሪም እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ዝቅተኛ የኢንተርኔት ተደራሽነት ባላቸው ሀገሮች፣ በድረገጾችና በማህበራዊ ትስስር ገጾች የሚደረጉ የዝንባሌ መለኪያዎች ዜጎችን ከነስብጥራቸው የመወከል አቅማቸው ዝቅተኛ ይሆናል። ይህም ማለት የምርጫ ዝንባሌ መለኪያ ውጤቱ የኢትዮጵያን ወይንም የአዲስ አበባን አልያም የመጠይቁ ትኩረት የሆነን አካባቢ ድምጽ ሙሉ ለሙሉ ላያሳይ ይችላል።

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ የመገናኛ ብዙሀን እና የጋዜጠኞች የምርጫ አዘጋገብ የስነምግባር እና አሰራር መመርያ አንቀፅ 22 ላይ ቅድመ ምርጫ ትንበያ ክልከላን በግልፅ አስቀምጧል። በዚህም መሰረት ማናቸውም የመገናኛ ብዙሀን ወይም ጋዜጠኛ የምርጫ ይፋዊ ውጤቱን ቦርዱ እስኪገልፅ ድረስ የምርጫ ውጤት ትንበያ ማድረግ ክልክል እንደሆነ አስቀምጧል።

በዚህ ዙርያ ለኢትዮጵያ ቼክ መረጃ የሰጠችው የቦርዱ የኮሚኒኬሽን ሀላፊ ሶልያና ሽመልስ “የውጤት ትንበያ ማድረግ ክልክል ነው። ይህን የሚያደርጉት ሚድያዎች ወይም የሲቪል ተቋማት ሲሆኑ መቆጣጠር ይቻላል፣ ግለሰቦች ማህበራዊ ሚድያ ላይ ሲያደርጉት ግን ያስቸግራል” ብላለች።

ስለዚህ በማህበራዊ ትስስር ገጾች የሚሰሩ የምርጫ ዝንባሌ መለኪያ ውጤቶችን በውሳኔዎቻችን ላይ ተጽዕኖ እንዳይፈጥሩ ማሰብ ያስፈልጋል።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::