“ዛሬ ምሽት የሲዳማ ክልል ልዩ ሀይል አባላት ይሸኛሉ። ሚድያዎች ተገኝተው ስለሚዘግቡ በግልፅ ታዩታላችሁ፣ በዛውም የዚህ የፌስቡክ ገፅ ወሬ ውሸት መሆኑ ይረጋገጣል”— የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ ለኢትዮጵያ ቼክ 

በዛሬው እለት “ማለዳ Media” የተባለ ከ119,000 በላይ ተከታይ ያለው የፌስቡክ ገፅ “የሲዳማ ክልል ልዩ ሃይል አባላት በሰሜኑ ጦርነት አንሳተፍም በማለት የሃዋሳ ካምፓቸውን ለቀው ወጡ” የሚል ዜና ይዞ ወጥቷል። ገፁ አክሎም “የልዩ ፖሊስ አባላት ወደ ቤተሰብ እና ዘመዶቻቸው ጋ በመበተናቸው ካምፕ ውስጥ የቀሩት ከ10 የማይበልጡ አመራሮች ብቻ መሆናቸው ታውቋል” ብሎ ፅፏል። 

በዚህ ዙርያ ኢትዮጵያ ቼክ ጉዳዩ የሚመለከተውን የሲዳማ ክልል አናግሯል። 

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ ለኢትዮጵያ ቼክ በስልክ እንዳሳወቁት መረጃው የሀሰት ነው፣ ዛሬ ምሽትም የሚሸኙ የክልሉ ልዩ ሀይል አባላት አሉ። 

“ይህን እና ሌሎች ተከታታይ የሀሰተኛ መረጃዎችን እዚህ ገፅ ላይ የሚፅፈው አሜሪካ ሀገር የሚኖር የሲዳማ ክልል ተወላጅ የሆነ ግለሰብ እንደሆነ መረጃ አለን። ይህም የሲዳማ ህዝብ ድጋፉን እንዳይሰጥ ለማድረግ የሚደረግ ጥረት ነው። ዛሬ የሚሸኙ አሉ፣ በፕሮግራሙ ላይ ተገኝተው ሚድያዎች ስለሚዘግቡ በግልፅ ታዩታላችሁ፣ በዛውም የዚህ የፌስቡክ ገፅ ወሬ ውሸት መሆኑ ይረጋገጣል” ብለዋል።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::