የኢንተርኔት መቋረጥ፣ የሀሰተኛ መረጃ ስርጭት እና መረጃ የማግኘት መብት!

የኢንተርኔት፣ በተለይ ደግሞ የማህበራዊ ሚዲያዎች መዘጋት እና መገደብ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ሀገራት እየተለመደ መጥቷል። ምርጫዎች ሲካሄዱ፣ የፖለቲካ አለመረጋጋቶች ሲከሰቱ፣ ግጭቶች ሲከሰቱ እንዲሁም ፈተናዎች ሲሰጡ እንዲህ አይነት መቋረጦች እየተለመዱ መጥተዋል።

ይህ ደግሞ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ የቴሌኮም ድርጅቶች በመንግስት ቁጥጥር ስር ባሉባቸው ሀገራት ይብሳል። በአብዛኛው እንደ ዋና ምክንያት ተደርጎ የሚቀርበው የሚከሰቱ አለመረጋጋቶችን ለመቀነስ እንዲሁም የፈተናዎች መሰረቅን ለመከላከል የሚል ነው።

በሌላ በኩል ከሰብዓዊ መብቶች አንፃር ሲታይ ደግሞ የዚህ አይነት የኢንተርኔት መዘጋት የሰዎችን ሀሳባቸውን የመግለጽ/የመናገር መብትን እና የሰዎችን መረጃ የማግኘት መብት ይጋፋሉ ተብለው ይታሰባሉ።
ኢትዮጵያ ውስጥ በተደጋጋሚ የኢንተርኔት መዘጋቶች እና የማህበራዊ ድህረገጾች መገደቦችን አይተናል። ለምሳሌ ያህል የአማራ ክልል ከፍተኛ አመራሮች በተገደሉ ጊዜ፣ ታዋቂው የአፋን ኦሮሞ ዘፋኝ እና አክቲቪስት ሀጫሉ ሁንዴሳ በተገደለ ጊዜ እና የተለያዩ ሀገራዊ ፈተናዎች በሚካሄዱበት ጊዜ የኢንተርኔት አገልግሎት ተዘግቶ ነበር። በነዚህ ጊዜያት ሁሉ ሰዎች ስለ ጉዳዮች መረጃን የማግኘት መብታቸው ተገድቦ ነበር።

በተለያዩ ጥናቶች ላይ እንደምናስተውለው ከሆነ የኢንተርኔት መዘጋት በትንሹም ቢሆን የሀሰተኛ መረጃ ስርጭትን ቢቀንስም በይበልጥ ግን ጉዳቱ እንደሚበልጥ እና የሰዎችን ሰብዓዊ እና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን እንደሚገድብ ለማየት ይቻላል። ከዛም በተጨማሪ ሰዎች ትክክለኛ መረጃን በትክክለኛው ሰዓት በማያገኙበት ጊዜ ወደራሳቸው የሴራ ትንታኔዎች እና ሀሳቦች ይገፋሉ፣ ይህም ስለጉዳዩ ትክክለኛውን መረጃ ቢያገኙ ከሚመጣው ጉዳት አንፃር ከፍተኛ ጉዳት ያስከትላል።

ኢንተርኔትን ከመዝጋት ይልቅ የማህበራዊ ትስስር ሚዲያዎችን በሚዲያዎቻቸው ላይ ስለሚሰራጩት መረጃዎች ሃላፊነት እንዲወስዱ ማድረግ እና ከተለያዩ የመረጃ ማጣራትን ስራ ከሚሰሩ ድርጅቶች ጋር እንዲሰሩ ማድረግ የተሻለ አማራጭ ነው። ከዛም በተጨማሪ ሰዎች ማህበራዊ ሚዲያን እንዴት መጠቀም እንዳለባቸው፣ በሁሉም ገጾች ላይ የሚወጣ መረጃ በጠቅላላ ትክክል አለመሆኑን እና እንደ እውነተኛ መረጃ ከመውሰዳቸው በፊት ማድረግ ስለሚገባቸው ማጣራት ማስተማር ግድ ይላል።

ከዚህ በተጨማሪ መንግስት በነዚህ የማህበራዊ ሚዲያዎች የሚሰራጩትን የሀሰተኛ መረጃዎች ለመዋጋት ማድረግ ካለበት ነገሮች አንዱ እና ዋናው ለህብረተሰቡ ትክክለኛ መረጃን በሰዓቱ ማቅረብ ነው። ይህንን ለማገዝ ደግሞ ሚዲያዎች የራሳቸው ሃላፊነት አለባቸው፣ ትክክለኛ መረጃን በሰዓቱ ለህዝቡ በማቅረብ። ህብረተሰቡ ትክክለኛ መረጃን በሰዓቱ ካገኘ ለሌሎች ሃሳቦች ተገዢነቱ ይቀንሳል።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::