የጎግል ካርታ መረጃን ሲጠቀሙ ሊያውቋቸው የሚገቡ ነጥቦች!

የጎግል ካርታ (Google Map) የቦታዎችን የሳተላይት ምስል፣ መንገዶችን፣ ድንበሮችን፣ የትራፊክ እንቅስቃሴዎችን ለማየትና በነሱም ለመጠቀም እንድንችል የሚረዱ አገልግሎቶችን ይሰጣል። የጎግል ካርታ እነዚህን አገልግሎቶች ለማቅረብ የሳተላይት ምስሎችን፣ ከመንግስታትና ከድርጅቶች የሚገኙ ኦፊሴላዊ ዳታዎችን፣ ከተጠቃሚዎች የሚላኩ ግብዐቶችንና ሌሎች የመረጃ ምንጮችን ይጠቀማል።

የጎግል ካርታ አድራሻዎችን በቀላሉ ለማወቅና ለሌሎች የዕለት ከዕለት ክንውኖችን ለማሳለጥ ከመጠቀም በዘለለ በግጭቶች ወቅት ስለተለዋዋጭ ሁኔታዎች የበለጠ ለመረዳትም አገልግሎት ላይ እናውለዋለን። በሀገራችንም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የግጭቶችን መቸት ለማወቅ በርከት ያሉ የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች የጎግልን ካርታ ሲያመሳክሩ ይስተዋላል። አንዳንዶቹ በቀጥታ የጎግልን ካርታ የሚመለከቱ ሲሆን ሌሎቹ በሌሎች ‘ኤዲት’ የተደረገን ይመለከታል።

‘ኤዲት’ የተደረጉ ካርታዎች ግጭቶችን እንከታተላለን በሚሉ ግለሰቦችና ቡድኖች በየጊዜው ‘አፕዴት’ የሚደረጉ ሲሆን የግጭቶችን ቀጠናና ማን የትኛውን አካባቢ ተቆጣጥሯል የሚለውን ለማሳየት ይሞክራሉ። ሆኖም ካርታዎቹን የሚሰሩ ግለሰቦችና ቡዱኖች መረጃዎችን ቀጥተኛ ባለሆነ መንገድ ከሚዲያዎች፣ ከመግለጫዎች፣ ከማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች እንዲሁም የራሳቸው ፍላጎት ካላቸው አክቲቪስቶች የሚሰበስቡ በመሆኑ ትክክለኛ ላይሆኑ ይችላሉ።

ሌላው የጎግልን ካርታ በምንጠቀምበት ወቅት ከምናመሳከርቸው ጉዳዮች መካከል ድንበሮች ይገኙበታል። የጎግል ካርታ የሀገሮችን፣ የክልሎችን፣ የዞኖችን፣ የወረዳዎችን እንዲሁም የከተማ አስተዳደሮችን ድንበሮች የሚያሳይ ቢሆንም ሙሉ ለሙሉ ትክክለኛ ናቸው ማለት አይቻልም። ጎግል በየጊዜው የሚቀርቡበትን ፖለቲካዊና ህጋዊ ቅሬታዎችና ክሶችን ተከትሎ ድንበሮች ሚስጥራዊና ጥንቃቄ በተሞላበት መንገድ መስራት መጀመሩ ቢነገርም አሁንም ጎላ ያሉ ስህተቶች ይታዩበታል።

በኢትዮጵያም ኢፊሴላዊ ከሆኑ ካርታዎች አንጻር በጎግል ካርታ ላይ የተሳሳቱ የውስጥ ድንበሮች አልፎ አልፎ ይታያሉ። አንዳንድ ሚዲያዎችም ከጎግል ካርታ የተወሰዱ የተሳሳቱ ድንበሮችን ሲጠቀሙ አስተውለናል። ስለሆነም በጎግል ካርታ የምናያቸው የክልል፣ የዞን፣ የወረዳና የከተማ አስተዳደር ድንበሮች ሙሉ በሙሉ ትክክለኛ ላይሆኑ ስለሚችሉ ከማጋራታችን በፊት መጠንቀቅ ይኖርብናል።

በጎግል ካርታ ላይ የሚታዩ መረጃዎች ትክክለኛ ናቸው ብለው ካለሰቡ በሚከተለው መልኩ ቅሬታ ማቅረብ ይችላሉ:-

1. የጎግል ካርታን መተግበሪያ ይክፈቱ
2. ቀጥሎ የጎግል አካውንት ፕሮፋይል ምስልዎን ይጫኑ
3. ከዚያም ‘Help & feedback’ የሚለውን ይጫኑ
4. ቀጥሎ የግብረ መልስ ምርጫውን (feedback option) ይምረጡ፣ በመጨረሻም መስተካከል አለበት የሚሉትን ስህተት በሚገባ አብራርተው ይጻፉ።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::