ሀሠተኛና የተዛቡ መልዕክቶች፣ የጥላቻ ንግግሮች፣ ሀሠተኛ አካውንቶችን በተመለከተ ምን ማድረግ እንችላለን?

ሀሠተኛና የተዛቡ መልዕክቶች፣ የጥላቻ ንግግሮች፣ ሀሠተኛ አካውንቶች እንዲሁም ኢንተርኔትን መሰረት ያደረጉ የማጭበርበር ድርጊቶች የሚያደርሱትን መጠነ ሰፊ ጉዳት ለመቀነስ እያንዳንዳችን የራሳችንን አስተዋጽዖ ማድረግ እንችላለን።

የመጀመሪያው ከላይ የተዘረዘሩትን ይዘቶች ላለማሰራጨትና ላለማጋራት መቆጠብ ሲሆን እንዲሁም እንዲህ ያሉ ይዘቶችን ከሚያሰራጩ አካላት እራስን ማራቅ ነው። በተጨማሪም አሉታዊ ይዘቶችንና አሰራጮችን ማጋለጥ፣ ለመረጃ አጣሪዎች ጥቆማ መስጠት፣ የራሳችንና በዙሪያችን ያሉ ሰዎችን የሚዲያ አጠቃቀም ንቃት ማጎልበት ትልቅ ለውጥ ማምጣት ያስችለናል።

ሌላኛው ለውጥ ማምጣት የሚያስችለን በጎ ተግባር በማህበራዊ ሚዲያ ገጾቻችን የሚያጋጥሙንን ሀሠተኛና የተዛቡ መልዕክቶችን፣ የጥላቻ ንግግሮችን፣ ሀሠተኛ አካውንቶችን እንዲሁም ኢንተርኔትን መሰረት ያደረጉ የማጭበርበር ድርጊቶችን ለማህበራዊ ሚዲያ አገልግሎት ሰጭ ኩባንያዎች ሪፖርት ማድረግ ነው።

እንደሚታወቀው የማህበራዊ ሚዲያ አገልግሎት ሰጭ ኩባንያዎች ከፖሊሲዎቻቸው ጋር የሚጣረሱ ይዘቶችን የሚከታተሉበትና የሚቆጣጠሩበት በሰው ሃይልና በቴክኖሎጂ የሚከወን አሰራር አላቸው። ሆኖም ከይዘቶቹና ከአሰራጮች ብዛትና ተለዋዋጭ ባህሪ አኳያ ብቻቸውን ድርጊቱን ይቆጣጠሩታል ተብሎ አይታሰብም። በየወቅቱ የሚወጡ የኩባንያዎቹ ሪፖርቶችና በባለሙያዎች የተሰሩ ይህንኑ ይነግረናል። ይህን ክፍተት ለመሙላትም ቀላል ግን ከፍ ያለ አስተዋጽዖ ማበርከት እንችላለን።

ለዚህም በማህበራዊ ሚዲያዎች የምንመለከታቸውን አሉታዊ ይዘቶችንና አሰራጮችን ሪፖርት በማድረግ በኩባንያዎቹ እይታ ውስጥ እንዲገቡና እርምጃ እንዲወሰድባቸው ጫና መፍጠር እንችላለን።

ምን አይነት ይዘቶችን ሪፖርት ማድረግ እንችላለን?

– በተወሰነ ቡድን ማንነት ላይ ያነጣጠረ፣ ብሔርን፣ ብሔረሰብንና ህዝብን፣ ሃይማኖትን፤ ዘርን፣ ጾታን ወይም አካል ጉዳተኝነትን መሰረት ያደረገና መድሎን ወይም ጥቃትን የሚያነሳሳ የጥላቻ ንግግርን

– ከላይ የተዘረዘሩትን ማንነቶች መሰረት አድርጎ በግለሰብ ላይ መድሎ ወይም ጥቃት የሚያነሳሳ የጥላቻ ንግግርን

– በተለይም በመሰራጨታቸው ምክንያት ጉዳት ሊያስከትሉ የሚችሉ ሀሠተኛና የተዛቡ መልዕክቶችን

– የተጽኖ ፈጣሪ ግለሰቦችንና ተቋማትን ስም በመጠቀም ተመሳስለው የተከፈቱ አካውንቶችንና ገጾችን እንዲሁም

– የማጭበርበርና የማታለል ድርጊቶችን ለመፈጸም ታስበው የሚሰራጩ ይዘቶችን ሪፖርት ማድረግ እንችላለን።

ከላይ የተዘረዘሩት ይዘቶች በጽሁፍ፣ በፎቶ፣ በድምጽ፣ በቪዲዮ፣ በስክሪን ቅጅ እና ወዘት ሊቀርቡ ይችላሉ። እንዲሁም ይዘቶቹን በአስተያየት መስጫ ቦታዎች (comment boxes)፣ ክፍት ወይም ዝግ በሆኑ ግሩፖች (public or closed groups)፣ በቀጥታ ስርጭቶች፣ በውስጥ መልዕክቶች (private messages) እና ወዘተ በኩል ልንመለከታቸው እንችላለን።

እነዚህን አሉታዊ ይዘቶች ሪፖርት ማድረግ በጣም ቀላልና በአጠረ ጊዜ መከናዎች የሚችል ነው። ምናልባት ከዚህ በፊት ሪፖርት አድርገው የማያውቁ ከሆነ ወይም ግር ካለዎ ኢትዮጵያ ቼክ ያዘጋጃቸውን እነዚህን አጠር ያሉ ቪዲዮዎች ይመልከቱ:

ፌስቡክ ላይ ሪፖርት ለማድረግ አማርኛ

ዩቱዩብ ላይ ሪፖርት ለማድረግ አማርኛ

ትዊተር ላይ ሪፖርት ለማድረግ አፋን ኦሮሞ

ቴሌግራም ላይ ሪፖርት ለማድረግ ትግርኛ

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::