የተነካኩ ወይም አውድ እንዲስቱ የሚሰሩ ቪድዮዎች እና መለያ መንገዶች!

በ2014 (እ.ኤ.አ.) ከተሸጡት የተንቀሳቃሽ ስልክ አይነቶች ውስጥ 55% የሚሆኑት ከተፈጠረ ሁለት አስርት ዓመታትን ያስቆጠረው የስማርትፎን ቴክኖሎጂ ያላቸው ስልኮች ነበሩ። ዛሬ ከአጠቃላይ የተንቀሳቃሽ ስልኮች ሽያጭ የስማርትፎን ድርሻ 78% ሆኗል። 

ተንቀሳቃሽ ስልክ ብቻ ግን አይደሉም፣ ከፍተኛ ጥራት ያለው ፎቶ እና ቪዲዮ ይቀርጻሉ። በኢንተርኔት መገናኘትን እና ለሌሎች ማጋራትን ይፈቅዳሉ፣ ያበረታታሉም። ይዘቶችን ይፈጥራሉ። ይዘቶችን ያሰራጫሉ። የመረጃ ቴክኖሎጂ ባለሙያዎች እነዚህን ይዘቶች ‘በተጠቃሚ የመነጩ ይዘቶች’ (user-generated contents) ይሏቸዋል። 

እኛም አገር፣ በተጠቃሚ የመነጩ ይዘቶችን በብዛት ማየት ከጀመርን ዓመታትን አስቆጥረናል። የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚነት መጨመርን ተከትሎም እነዚህ ይዘቶች በስፋት ይሰራጫሉ፣ ሐሰተኛ እና አሳሳች የቪድዮ ይዘቶችም በየድረ ገጹ ይዘዋወራሉ። እነዚህን ቪድዮዎች የሚያይ፣ አይቶም የሚያምን ሰው እስካለ ድረስም በሰፊው መሰራጨታቸውን ይቀጥላሉ። ይህንን ለመግታት ታዲያ ማየት ማመን ነው የሚለውን ዘመን ተሻጋሪ አባባል በድጋሚ ማጤን ያስፈልጋል። 

ከሩቅ ሲታይ፣ ሐሰተኛ ቪድዮዎችን መለየት እጅግ አስቸጋሪ ተግባር ሊመስል ይችል ይሆናል። በመሰረቱ ግን ሐሰተኛ ቪድዮዎችን መለየት ምንነታቸውን ከማወቅ ይጀምራል። 

በቀላል ቋንቋ ሐሰተኛ ቪድዮ ማለት የተነካካ ቪድዮ ማለት ነው። አውዱን እንዲያጣ/እንዲስት ሆኖ የተቆረጠ ቪድዮ፣ አሳሳች አርትዖት እንዲሁም ተንኮል አዘል ለውጥ የተደረገበት ቪድዮ ሐሰተኛ ሊባል ይችላል። 

ሁሉም የተቆረጠ ወይም የአርትዖት ስራ የተሰራበት ቪድዮ ሐሰተኛ ቪድዮ ነው ማለት ግን አይደለም። ሆኖም በመቆረጡ ምክንያት ከአውዱ ውጭ የሆነ ትርጓሜን የሚፈጥር ከሆነ ወይም ከቪድዮው ላይ የተቀነሰ/የተጨመረ ነገር ሲኖር፣ ይህ ቪድዮ ሐሰተኛ የመሆን እድሉ ከፍተኛ ነው። ይህ ተግባር ከዚህ በታች ያሉትን ያጠቃልላል: 

* አንድን ጉዳይ በስህተት ማስቀመጥ (Misrepresentation)

* የተወሰነውን የቪድዮ ክፍል ነጥሎ ማውጣት ወይም ቆርጦ ማስወገድ

* የቪድዮውን የተለያዩ ክፍሎች ቆርጦ መቀጣጠል

* የቪድዮውን መጠን (ቁመት እና ጎን) መቀየር

* የቪድዮውን ፍጥነት፣ የፍሬም ፍጥነት (frame rate)፣ ድምፅ እና ሌሎች መረጃዎችን መቀየር

* በቪድዮው ላይ ማንኛውም ‘የቀዶ-ጥገና’ (Doctoring) ስራ መስራት

* በኮምፒውተር ፈጠራ የተሰራን ምስል ወይም የምስል ክፍልን በቪድዮው ላይ መጠቀም (fabrication using artificial intelligence) 

ልምድ ያላቸው አይኖች አንድ ቪድዮ ከተቀረጸ በኋላ የተፈጠሩ (የተጨመሩ ወይም የተቀነሱ) ልዩነቶችን መለየት አይቸገሩም። ጥሩው ነገር ብዙ ልምድ የሌለው ሰው በቪድዮዎች ላይ ከቀረጻ በኋላ የተፈጠሩ ልዩነቶችን አንጥሮ ለመለየት InVID የተባለውን ተሰኪ (Plugin) በክሮም ወይም ፋየርፎክስ አሳሾች (Chrome Firefox browsers) ላይ በማከል በቀላሉ መጠቀም መቻሉ ነው። 

InVID ለዩትዩብ፣ ፌስቡክ እና ትዊተር ቪድዮዎች የተጎላበተ የሜታዳታ መመልከቻ (metadata viewer) ነው። ይህ ተሰኪ (Plugin) በነጻ የሚገኝ ሲሆን አንዴ ከተጫነ በኋላ ስምንት የተግባር አዝራሮችን (buttons) በአሳሹ ላይ ይፈጥራል። ሁሉም አዝራሮች ከላይ የተጠቀሱትን ከቀረጻ በኋላ በቪድዮው ላይ የተፈጠሩ ልዩነቶችን ለመለየት የተለያየ ዘዴዎችን ይጠቀማሉ። ሐሰተኛ ቪድዮ የመለየት ስራንም በእጥፍ ያቃልላሉ። 

ዝርዝር ትምህርታዊ ቪድዮዎችን በገጹ የላይኛው ረድፍ ላይ ካሉት አዝራሮች ውስጥ “Tutorial” የሚለውን በመጫን ሊያገኟቸው ይችላሉ። 

https://www.invid-project.eu/tools-and-services/invid-verification-plugin/ 

በተጨማርሪም በInVID ላይ የሰራነውን መሰረታዊ የማሳያ ቪድዮም በዩትዩብ ቻናላችን ላይ እንድትመለከቱት እንጋብዛለን። 

https://www.youtube.com/watch?v=2qDKs5CLEjQ 

መልካም ማጣራት!

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::