በዩትዩብ ቻናሎች የሚተላለፉ መረጃዎችን ከማመናችን በፊት ልንጠይቃቸው የሚገቡ ነጥቦች!

ከሳምንት በፊት ከ46 አገራት የተውጣጡ 80 የመረጃ አንጣሪ (አጣሪ) ተቋማት ዩትዩብ ሀሠተኛና የተዛቡ መረጃዎችን ስርጭት በመግታት ረገድ አሳይቶታል ያሉትን ቸልተኝነት በተመለከተ ለድርጅቱ ደብዳቤ ጽፈዋል። ኢትዮጵያ ቼክም የደብዳቤውን ይዘት አጋርቶ ነበር።

ተቋማቱ በጻፉት ደብዳቤ ዩትዩብ ሀሠተኛና የተዛቡ መረጃዎችን ለሚያሰራጩ እንዲሁም ሴራ ለሚተነትኑ ግለሰቦችና ቡድኖች ዋነኛ መናኸሪያ ሆኖ መቀጠሉ እንዳሳሰባቸውና “ሀላፊነት የጎደላቸው ግለሰቦችና ቡድኖች በተጠቃሚዎች ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እንዲያደርጉ እንዲሁም እንዲደራጁና ገንዘብ እንዲሰበስቡ ፈቅዷል’’ የሚል የሰላ ትችት አቅርበዋል።

ወደ ሀገራችን ስንመጣም በተለይ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በርካታ የዩትዩብ ቻናሎች ተከፍተው መረጃ፣ ትንታኔ፣ ቃለምልልስ እና ሌሎች ይዘቶችን ሲያጋሩ ይስተዋላል። እነዚህ የዩትዩብ ቻናሎች የሚያጋሯቸውን ይዘቶች በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች እንደሚመለከቷቸውም መታዘብ ችለናል። ይህም ዩትዩብ ለብዙ ሰዎች ዋነኛ የመረጃ ምንጭ መሆኑን ያመለክታል።

ምንም እንኳን መረጃና ሌሎች ይዘቶችን የሚያጋሩ የዩትዩብ ቻናሎች መበራከት ከአማራጭነትና ከሀሳብ ብዝሃነት አኳያ የራሱ አዎንታዊ ጎን ቢኖረውም ለሀሠተኛና የተዛቡ መርጃዎች ስርጭት በር ሊከፍት ስለሚችል በነዚህ ቻናሎች የሚተላለፉ መረጃዎችና ትንታኔዎችን ከማመናችን በፊት ቆም ምብሎ ማሰብና የሚከተሉትን ጥያቄዎች መጠየቅ ያስፈልጋል:

የዩትዩብ ቻናሉ በራሱ ዘጋቢዎች የተሰሩ ‘ኦርጅናል’ መረጃዎችን ያቀርባል?

የዩትዩብ ቻናሉ ለሚያቀርባቸው መረጃዎች በግልጽ የሚታወቁ ምንጮችን ይጠቅሳል?

በዩትዩብ ቻናሉ የሚሰራጩ መርጃዎች እንደ ሚዛናዊነት፣ ትክክለኛነት፣ አካታችነት ወዘት ያሉ የጋዜጠኝነት የሙያና የስነምግባር መርሆች ይታዩባቸዋል?

የዩትዩብ ቻናሉ ለስህተቶች ፈጣንና ግልጽ ዕርምት ይወስዳል?

የዩትዩብ ቻናሉ በግልጽ የሚታወቅ አድራሻ አለው? የአዘጋጆቹ ማንነት ይታወቃል?

የዩትዩብ ቻናሉ ለስህተቶች ፈጣንና ግልጽ የዕርምት ዕርምጃ ይወስዳል?

ከላይ ለተዘረዘሩት ጥያቄዎች ያገኘነው ምላሽ በአመዛኙ አሉታዊ ከሆነ የዩትዩብ ቻናሉ ለሀሠተኛና ለተዛቡ መርጃዎች ሊያጋልጠን ስለሚችል ቆም ብለን ማሰብና መረጃ የምናገኝበት አማራጭ ማስተካከል ይጠበቅብናል።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::