ተመሳስለው የሚከፈቱ የትዊተር አካውንቶችን ለመለየት እንዲችሉ እነዚህን ነጥቦች ያስተውሉ! 

ባለፉት ጥቂት ወራት ኢትዮጵያን በተመለከተ በሚደረጉ የትዊተር መስተጋብሮች ላይ ተጽዕኖ በመፍጠር ረገድ ፈረንጅ/ምዕራባዊ በመምሰል የሚከፈቱ አካውንቶች ይጠቀሳሉ። እነዚህ አካውንቶች በአጭር ጊዜ በርካታ ተከታይ ሲያገኙ የሚስተዋል ሲሆን ሀሠተኛና የተዛቡ መረጃዎችንም በማስራጨት በግንባር ቀደምነት ይጠቀሳሉ። እርስዎም እንደዚህ ባሉ ሀሠተኛ አካውንቶች ተጽዕኖ ስር ላለመውደቅ ከመከተለዎና መልዕክቶቻቸውን ከማጋራትዎ በፊት የሚከተሉትን ምርመራዋች ይከውኑ: 

– የፕሮፋይል ስምንና የማንነት ገላጭ ጽሁፍን (Bio) በጥንቃቄ ይመልከቱ፣ አሠሳ (search) ያድርጉ። 

– ተጽዕኖ ለመፍጠር የሚሹ ሀሠተኛ የትዊተር አካውንቶች የምዕራባውያንን ስም መጠቀም የሚመርጡ ሲሆን በማንነት ገላጭ ጽሁፋቸው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት፣ የታላላቅ ዩኒቨርስቲዎች፣ የምርምር ተቋማት ወዘተ ሠራተኞች እንደነበሩ ይገልጻሉ። እንደዚህ አይነት አካውንቶች ሲመለከቱ ስማቸውንና በማንነት ገላጭ ጽሁፋቸው የተጠቀሱ ተቋማትን በመጠቀም አሠሳ ያድርጉ። እውነተኛ ከሆኑ በተቋማቱ ድረገጾች፣ በሊንክድኢን (LinkedIn) ወይንም በሌሎች ድረ-ገጾች ላይ ያገኟቸዋል። 

– የፕሮፋይል ስሙንና የአካውንቱን URL ስምረት ይመርምሩ። በአብዛኛው እውነተኛ አካውንቶች የፕሮፋይል ስማቸውና የአካውንት URL ስምረት ይኖረዋል። በአንጻሩ በርከት ያሉ ሀሠተኛ አካውንቶች ስማቸውን በየጊዜው የመቀያየር ልምድ ስላላቸው የፕሮፋይል ስማቸውና የአካውንት URL ስምረት የተዘባ ሊሆን ይችላል። ለምሳሌ በሀሠተኛነት የጠረጠሩት አካውንት የፕሮፋይል ስሙ ‘Jhon Anderson’ ከሆነና የአካውንቱ URL  “twitter.com/belete-gedamu” የሚል ከሆነ ሀሠተኛ የመሆን ዕድሉ ከፍ ያለ ስለሚሆን ጥንቃቄ ያድርጉ። 

– የፕሮፋይል ምስላቸው እውነተኛ ስለመሆኑ ያጣሩ።  ተጽኖ ለማድረግ በመሻት የሚከፈቱ ሀሠተኛ የተዊተር አካውንቶች በሰው መሰል ፊቶች (fake-face) አምራች ድረ-ገጾች የተመረቱ ፎቶዎችን ወይንም የሌላ ሰው ምስል ይጠቀማሉ። ጎግል ሪቨርስ ኢሜጅ ሰርች (Google Reverse Image Search)፣ ቲንአይ (Tineye)፣ ያንዴክስ (Yandex) እና ሌሎችን ሪቨርስ ኢሜጅ ፈላጊ መተግበሪያዎችን በመጠቀም የፎቶውን ትክክለኛነት ለማረጋገጥ ይሞክሩ። 

– አካውንቱ የተከፈተበትን ጊዜ ይመልከቱ። ብዙዎቹ ተጽዕኖ ለመፍጠር የሚሹ ሀሠተኛ የትዊተር አካውንቶች በቅርብ የተከፈቱ የመሆን ዕድላቸው የሰፋ ሲሆን አንዳንዶቹ የቆዩም ሊሆኑ ይችላሉ። ከወራት ወይንም ከሳምንታት በፊት የተከፈቱና ተሳትፏቸው ጎላ ያለ አካውንቶች ከሆኑ እውነተኛ ላይሆኑ ስለሚችሉ ይጠንቀቁ። በአንጻሩ አካውንቶቹ ከዓመታት በፊት የተከፈቱ ከሆኑ ተጨማሪ ማጣራት ያድርጉ። አካውንቶቹ ስም አለመቀየራቸውን፣ ተሳትፎ የሚያደርጉበት መጠን በጊዜ ሂደት አለመቀየሩን ወዘተ ይመርምሩ። 

– በተጨማሪም የፕሮፋይል ስማቸውንና የትዊተር ሃንድላቸውን (username/handle) ስምረት፣ የተከታዮቻቸውን ብዛትና ማንነት፣ የሚከተሏቸውን ሰዎችና ተቋማት ማንነት፣ የሚያጋሯቸው መልዕክቶች ጥራትን (tweet quality) ወዘተ ስለአካውንቱ እውነተኛነት ወይንም ሀሠተኛነት የሚነግረን ነገር ስለሚኖር በጥንቃቄ ይመርምሩ። 

– እንደ ቦቶሜትር (Botometer) ያሉ የትዊተር አካውንት እንቅስቃሴና መረጃ የሚጠቁሙ መተግበሪያዎችን መጠቀምም ስለ አካውንቱ የበለጠ ለማወቅ ይረዳል። እነዚህ መተግበሪያዎች ስለ አካውንቱ እንቅስቃሴ ጊዜና ቦታ፣ የሃሽታግ አጠቃቀም፣ የተከታዮች ማንነት፣ የቋንቋ ምርጫ ወዘተ በቂ መረጃ ይሰጣሉ። አንዳንዶቹ መተግበሪያዎች እንቅስቃሴውን በማጤን የአካውንቱን ትክክለኛነት በቁጥር ይመዝናሉ።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::