ከኢንተርኔት ቴክኖሎጂ በተለይም ከማህበራዊ ሚዲያ መስፋፋት ጋር ተያይዞ ከተከሰቱ ነገሮች መካከል ዜና የምናገኝባቸው አማራጮች መስፋት በዋነኝነት ይጠቀሳል!

ለዓመታት በመንግስታት ወይም በጥቂት የግል ሚዲያ ተቋማት ተይዞ የነበረው የመረጃ ‘ሞኖፖሊ’ የተፍታታ (libralise) ሲሆን አሁን ላፕቶፕ ኮምፕዩተር ወይንም ዘመናዊ ስልክና የኢንተርኔት ግንኙነት ያለው ቡድን ወይም ግለሰብ ከመረጃ ተጠቃሚነት ባሻገር የመረጃ አምራችና አሰራጭ የመሆን ዕድል ተፈጥሮለታል።

ይህንን ዕድል በመጠቀም የመረጃ አምራችና አሰራጭ ከሆኑት መካከል “ዜና አሰባሳቢዎች” ወይም በእንግሊዘኛው ‘News Aggregators’ ይገኙበታል። ዜና አሰባሳቢዎች ከማህበራዊ ሚዲያዎች፣ ከድረ-ገጾች ወይም ከመደበኛ ሚዲያዎች አልያም በስማ በለው የሰበሰቡትን መረጃ ሰብስበውና አደራጅተው ለተከታታዮቻቸው የሚያቀርቡ ናቸው።

ይህ አሰራር ከሚሊኒየሙ መባቻ ጀምሮ በመላው ዓለም የተለመደ ሲሆን በርካታ ተቋማትና ግለሰቦችም በዚህ ስራ ተሰማርተው ይገኛሉ። የሌሎች ሀገራት ልምድ እንደሚያሳየው በመደበኛነት ይህን ስራ የሚከውኑ ተቋማት መረጃ ለወሰዱባቸው ሚዲያዎች እውቅና (credit) የሚሰጡ ሲሆን ወደ ዋናው ዜና የሚያደርስ ማስፈንጠሪያም (link) ያስቀምጣሉ።

ወደ ሀገራችን ስንመጣ በርካታ ዜና አሰባሳቢ የሚዲያ ተቋማትና ግለሰቦች መኖራቸውን መታዘብ የሚቻል ሲሆን በስፋት በዩትዩብ እንዲሁም በቴሌግራምና በሌሎች የማህበራዊ ሚድያ መተግበሪያዎች ያሰባሰቡትን መረጃ ያሰራጫሉ።

ኢትዮጵያ ቼክ ባደረገው ዳሰሳ አብዛኞቹ ኢትዮጵያን በተመለከተ መረጃ የሚያሰራጩ ዜና አሰባሳቢዎች መረጃ ለወሰዱበት ሚድያ እውቅና የማይሰጡ፣ ምንጭ የማይጠቅሱ፣ እንዲሁም ወደ ዋናው ዜና የሚያደርሱ ማስፈንጠሪያወችን የማያያዙ መሆናቸውን ተመልክቷል።

እነዚህ ዜና አሰባሳቢዎች ከዚህም ከዚያም የሰበሰቧቸውን መረጃዎች “የዕለቱ ዋና ዋና ዜና”፣ “የዕለቱ አበይት ዜናዎች” ፣ “አሁናዊ መረጃዎች”፣ “ሰበር ዜና”፣ ወዘተ የሚሉ ርዕሶችን በመጠቀም እንደሚያደራጁ መታዘብ ችለናል። ለዜናዎቹ ማጀቢያም በተመሳሳይ ከዚህም ከዚያም የተሰበሰቡ ፎቶዎችንና ቪዲዮዎችን የሚጠቀሙ ሲሆን ምንጫቸውን አይጠቅሱም።

አንዳንዶቹ ዜና አሰባሳቢዎች ምንም እንኳን ለሚያቀርቧቸው መረጃዎች ተገቢ የሆነ ምንጭና እውቅና ባይሰጡም ሪፖርተር ቀጥረው፣ ዜና ከምጩ ሰብስበውና አደራጅተው ከሚያቀርቡ ሚዲያዎች በላይ በርካታ ተከታታይ እንዳላቸው አስተውለናል። ይህም ለሀሠተኛና የተዛባ መረጃ ስርጭ የራሱን አስተዋጾ እንደሚያበረከት መገመት ይቻላል።

ስለሆነም መረጃ ለወሰዱበት ሚዲያ እውቅና የማይሰጡ፣ ምንጭ የማይጠቅሱ፣ ወደ ዋናው ዜናው የሚያመራ ማስፈንጠሪያ የማያያይዙ ዜና አሰባሳቢዎች ለሀሠተኛና ለተዛባ መረጃ ሊያጋልጡን ስለሚችሉ ጥንቃቄ እናድርግ።

ሁሌም ምንጩ በግልጽ ያልተጠቀሰ መረጃ ስንሰማ ወይም ስናነብ ቆም ብለን እናስብ፣ መረጃውን ለማጣራትም እንጣር።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::