ማህበራዊ ሚድያዎችን በመጠቀም ተፅእኖ ለመፍጠር የሚደረጉ የሀገራት ሙከራዎች!

ባለፈው ሳምንት አጋማሽ ፌስቡክ ይፋ ባደረገው ሪፖርት መቀመጫቸውን ግብጽ በማድረግ በኢትዮጵያ፣ በሱዳንና በቱርክ ላይ ያነጣጠሩ 17 የፌስቡክ አካውንቶችን፣ 6 ገጾችን እንዲሁም 3 የኢንስታግራም አካውንቶችን ማስወገዱን አስታውቋል።

እንዲወገዱ ከተደረጉት ገጾች መካከል አንደኛው በኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ላይ ትችት ያቀርብ እንደነበር ተገልጿል።

ፌስቡክ ይህን ያስታወቀው በዚህ ዓመት መጋቢት ወር ላይ “የተቀናጀ ሐሠተኛ ባህሪያት” (coordinated inauthentic behavior) በሚል ባወጣው ሪፖርት ነው። ድርጅቱ “የተቀናጀ ሐሠተኛ ባህሪያት” በማለት የሚጠራውን ሪፖርት ማውጣት የጀመረው እ.አ.አ በ2014 ዓም ነበር። ትዊተር በኩሉ እንዲህ ያሉ ሪፖርቶችን “በመንግስት የሚደገፉ የመረጃ ተልዕኮዎች” (state-backed information operations) በሚል ስያሜ እ.አ.አ ከ2017 ዓ.ም ጀምሮ ይፋ ያደርጋል።

ሁለቱ የማህበራዊ ሚዲያ አንቀሳቃሾች ባለፉት ሁለት ዓመታት ብቻ 147 ሐሠተኛ ተጽዕኖ ፈጣሪ ተልዕኮዎችን የተመለከቱ ሪፖርቶችን ይፋ ያደረጉ ሲሆን በዚህም በሺህዎች የሚቆጠሩ አካውንቶችንና ገጾችን ዘግተዋል።
ከላይ በተጠቀሱት ሪፖርቶች የሚካተቱት ሐሠተኛ ተልዕኮ አስፈጽሚ አካውንቶችና ገጾች በአብዛኛው ሀገሮች ስትራቴጅያዊ ግባቸውን ለማሳለጥ በሌላ ሀገር የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ለመግባት የሚከፍቷቸውና የሚደግፏቸው ናቸው።

እነዚህ በተቀናጀና በተደራጀ መልኩ የሚንቀሳቀሱ የውጭ መንግስት ሐሠተኛ ተልዕኮ አስፈጽሚ አካውንቶችና ገጾች የተዛቡ መረጃዎችን በማሰራጨት ኢላማ በተደረጉ ሀገሮች ጤናማ የማህበራዊ፣ የምጣኔ ሀብትና የፖለቲካ እንቅስቃሴ እንዳይኖር ይሰራሉ። ኢላማ በተደረጉ ሀገሮች የሚገኙ የፖለቲካ ልዩነቶችን በማጦዝ ልዩነቶች እንዲሰፉ ያደርጋሉ። ዜጎች በተቋሞቻቸው ላይ እምነት እንዲያጡ በመቀስቀስ ስርዐት አልበኝነትን ያነግሳሉ። በብሔሮች፣ በዘሮች፣ በሀይማኖቶች፣ በመደቦች ወዘተ መካከል ያሉ ልዩነቶችን በመቦርቦር ግጭች ይፈጥራሉ።

የውጭ መንግስት ሐሠተኛ ተልዕኮ አስፈጻሚ አካውንቶችና ገጾች በተለይ ኢላማ በተደረጉ ሀገሮች ምርጫ በሚደረግበት ወቅት ሐሠተኛና የተዛቡ መረጃዎችን በማሰራጨት ዜጎች በእውቀት ላይ የተመሰረተ ውሳኔ የሚያሳልፉበት ሂደትን ለማወክ ይንቀሳቀሳሉ። እ.አ.አ በ2014 ዓ.ም በአሜሪካ በተደረገው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ የሩሲያ መንግስት ሐሠተኛ ተልዕኮ አስፈጽሚ አካውንቶችና ገጾችን በስፋት በመጠቀምና በመደገፍ ጣልቃ ስለመግባቱ በስፋት የተዘገበበት እውነት ለዚህ ማሳያ ይሆናል።

ቀደም ባሉት ዓመታት የውጭ መንግስት ሐሠተኛ ተልዕኮ አስፈጽሚ አካውንቶችና ገጾች በሀገሮች የስለላ ወይንም የውጭ ጉዳይና የስትራቴጅ ተቋማት የሚዘውሩ መሆናቸውን የጥናት ሪፖርቶች የሚጠቁሙ ሲሆን ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ግን ሙያው ባላቸውና ከመንግስታት ዳጎስ ያለ ክፍያ በሚከፈላቸው የሶስተኛ ወገን የህዝብ ግንኙነት ተቋማት (public relations firms) የሚንቀሳቀሱ ስለመሆናቸው ፌስቡክና ትዊተር ከሚያወጧቸው ሪፖርቶች መረዳት ይቻላል። ይህም መንግስታት ራሳቸውን ከተጠያቂነት ለማሸሽ ይረዳቸዋል።

የውጭ መንግስት ሐሠተኛ ተልዕኮ አስፈጽሚ አካውንቶችና ገጾች ኢላማ በተደረው ሀገር የማህበራዊ ትስስር ምህዳር ሰርገው ለመግባት የረቀቁ ዘዴዎችን የሚጠቀሙ ሲሆን በአብዛኛው በዜና አሰራጭነት (news media)፣ በአራማጅነት (activist)፣ በተንታኝነት እንዲሁም መንግስታዊ ባለሆነ ድርጅትነት ራሳቸውን ያስተዋውቃሉ። ከዚህ በተጨማሪም አወናባጆች (trolls) እና ቦቶች በስፋት ጥቅም ላይ ይውላሉ። የፕሮፋይል መስላቸውም ሰንደቅ አላማ፣ የብሔር ወይንም የፖለቲካ ቡድን አርማ እንዲሁም በሰው ሰራሽ አስተውሎ (Artificial Intelligence) የተፈበረኩ ሰው መሰል ፊቶችን ይጠቀማሉ። ይህም በቀላሉ ሰርገው ለመግባት ረዳቸዋል።

የውጭ መንግስት ሐሠተኛ ተልዕኮ አስፈጽሚ አካውንቶችና ገጾች ለመለየት አስቸጋሪ ሲሆን ፌስቡክና ትዊተር በባለሙያና በሰው ሰራሽ አስተውሎ የማህበራዊ ትስስር ገጽ አጠቃቀም ባህሪያቸውን በማጥናት ያስወግዳሉ። እነዚህ አካውንቶችና ገጾች ተልዕኳቸውን ሲጨርሱ ወይንም ሐሰተኛነታቸው እንዳይታወቅ በየጊዜው ስም የመቀየር ባህሪ ያላቸው ሲሆን ፌስቡክ ይህን ለተጠቃሚዎች ግልጽ ለማድረግ የገጽ ድህረ-ታሪክ (page history) አገልግሎት ይሰጣል።

አካውንቶቹና ገጾቹ ብዙ ተከታይ ለማፍራት ራሳቸውን በክፍያ የሚያስተዋውቁ ሲሆን ፌስቡክና ትዊተር የማስታወቂያ ክፍያን ግልጽነትን በመተግበር የገጹ ተከታዮች ክፍያውን የፈጸመውን ወገን ለማወቅ እንዲችሉ ያደርጋሉ።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::