የሀሰተኛ መረጃ ስርጭትን ለመከላከል ሀገራት እየወሰዷቸው የሚገኙ እርምጃዎች! 

የሀሰተኛ መረጃ ስርጭት አዲስ ነገር አይደለም። ይሁንና የኢንተርኔት ብሎም የማህበራዊ ሚድያ መፈጠር የስርጭቱን ፍጥነት እጅግ ጨምሮታል። 

ይህንን ችግር ለመቋቋም በርከት ያሉ ሀገራት የሀሠተኛ የመረጃ ስርጭትን ለመቆጣጠር ያስችላሉ ያሏቸውን የተለያዩ እርምጃዎችን ሲወስዱ ታይተዋል፣ አዲስ ህጎችንም አውጥተዋል። የአንዳድ ሀገራት ህጎች ሀሠተኛ መረጃ የሚያሰራጩ ግለሰቦችን ተጠያቂ የሚያደርጉ ሲሆኑ አንዳንዶች ደግሞ እንደ ፌስቡክ እና ትዊተር የመሳሰሉ የማህበራዊ ሚዲያ ተቋማትን ይቀጣሉ፣ ሌሎቹ ደግሞ ሁለቱንም። 

በአለማችን ውስጥ የሀሰተኛ መረጃን ለመከላከል ከወጡ ህጎች ውስጥ የሚከተሉት ይገኙበታል: 

  ሲንጋፖር

ሲንጋፖር የማህበራዊ ሚዲያ ድርጅቶችን ተጠያቂ የሚያደርግ ህግ አውጥታላች። ይህም መንግስት ሃሰተኛ ናቸው ብሎ የያዛቸውን ልጥፎች እንደ ፌስቡክ ያሉ ድርጅቶች ወዲያው ማስጠንቀቂያ እንዲሰጡ ያዛቸዋል። ይህንን ጥሶ የሚገኝ አካል ደግሞ እስከ 737,500 ዶላር እና የ10 አመት እስራት ይጠብቀዋል። 

  ሩሲያ

የሩሲያው ፕሬዘዳንት ቭላድሚር ፑቲን ባስወጡት ህግ መሰረት የሀገሪቱ ህግ እንደ ሀሰተኛ ዜና ይቆጠራል ያለውን ዜና ማስጠንቀቂያ ይሰጣል፣ ይህንን ማስጠንቀቂያ ተላልፎ የሚገኝ አካል ግን ድረ-ገጹ እንደሚዘጋ እና ግለሰቦች ከሆኑ ደግሞ 6,109 ዶላር እንደሚቀጡ ይደነግጋል። 

  ፈረንሳይ

ፈረንሳይ ደግሞ ሁለት የጸረ-ሀሰተኛ መረጃ ህጎችን አጽድቃለች። በተለይ ደግሞ እነዚህ ህጎች የወጡት በ2017ቱ የፈረንሳይ ምርጫ ወቅት የሩሲያ ጣልቃ ገብነት ነበር የሚሉ ክሶች መቅረብ ከጀመሩ በሗላ ነበር። 

  ኢትዮጵያ

የጥላቻ ንግግር እና የሐሰተኛ መረጃ ስርጭትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ተብሎ አዋጅ ወጥቷል። አዋጁ አላማው ሰዎች ሀሳብን በነፃነት የመግለጽ መብታቸውን ሲጠቀሙ ግጭት ወይም ሁከትን የሚቀሰቅስ ወይም ብሔርን፣ ሃይማኖትን፣ ዘርን፣ ጾታን ወይም አካል ጉዳተኝነትን መሰረት በማድረግ በግለሰብ ወይም በተለየ ቡድን ላይ ጥላቻ ወይም መድልዎ ከሚያስፋፋ ንግግር ከማድረግ እንዲቆጠቡ ታስቦ የወጣ አዋጅ ነው። የጥላቻ ንግግር ወይም የሐሰተኛ መረጃ ስርጭት ወንጀሉ የተፈጸመው ከ5,000 በላይ ተከታይ ባለው የማህበራዊ ሚዲያ ገጽ ከሆነ ወይም በብሮድካስት አገልግሎት ወይም በየጊዜው በሚወጣ የህትመት ውጤት ከሆነ ቅጣቱ እስከ ሶስት አመት የሚደርስ ቀላል እስራት እና ከብር 100,000 ያልበለጠ መቀጮ ይሆናል። 

እነዚህ ህጎች በወጡ ጊዜ ብዙዎች ቅሬታቸውን አሰምተዋል፣ የህጎቹ መውጣት የሀሳብን በነፃነት የመግለፅ ነፃነትን ይገድባል የሚሉ ስጋቶች ተንፀባርቀዋል።

በአንጻሩ እንደ ፊንላንድ እና ስዊድን የመሳሰሉት ሀገራት ዜጎቻቸውን በማስተማር እና በማንቃት የሀሰተኛ መረጃ ስርጭትን ለመቀነስ እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ። 

በአለማችን ላይ ያሉ ሀገራት በሀሰተኛ መረጃ ስርጭት ዙሪያ ያወጧቸውን ህጎች፣ መመሪያዎች እና እርምጃዎችን ለማንበብ፡ https://www.poynter.org/ifcn/anti-misinformation-actions/

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::