የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች አልፎ አልፎ በግለሠቦች ወይንም በተቋማት ገጾች የተለጠፉ መረጃዎችን በቀጥታ ከማጋራት ይልቅ የስክሪን ቅጅዎችን (screenshots) መጠቀም ይመርጣሉ። 

ለምርጫቸው ብዙ ምክንያቶች ይኖራሉ። ለምሳሌ በትዊተር አካውንቶች የተለጠፉ መረጃዎችን የፌስቡክ ተጠቃሚ ለሆኑ ተከታዮች ለማጋራት ስክሪን ቅጅ መውሰድ አንድ አማራጭ ሊሆን ይችላል። 

ሆኖም በማህበራዊ ትስስር ገጾች የምንመለከታቸው የስክሪን ቅጅዎች ሁሉ እውነተኛ ናቸው ማለት አይደለም። አንዳንዶቹ ቅጅዎች ሀሠተኛ መረጃን በሚያሰራጩ አካላት የተቀናበሩ ሊሆኑ ይችላሉ፣ ይህንን ለመከወን የሚያስችሉም በርካታ ነጻ መተግበሪያዎች ይገኛሉ። 

በሀገራችንም የተቀናበሩ የስክሪን ቅጅዎችን በመጠቀም ሀሠተኛና የተዛቡ መረጃዎችን ማሰራጨት በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየጨመረ መምጣቱን አስተውለናል። ኢትዮጵያ ቼክም እንዲህ ያሉ ድርጊቶችን በተደጋጋሚ ማጋለጡ ይታወቃል።

ስለሆነም የስክሪን ቅጅዎችን በመጠቀም የተጋሩ መረጃዎችን በማህበራዊ ትስስር ገጾች ስንመለከት ቆም ብሎ ማሰብ፣ መመርመርና ማጣራት ያፈልጋል። የስክሪን ቅጅዎችን ትክክለኛነት ለማረጋገጥ ከምንጠቀምባቸው ዘዴዎች ዋነኛው ቅጅው ተወሰደ ወደ ተባለበት የማህበራዊ ትስስር ገጽ በማምራት ማመሳከር ነው። ለምሳሌ ስክሪን ቅጅው ከአቶ “ሀ” የፌስ ቡክ ገጽ ተወስዷል ከተባለ፣ ወደ አቶ “ሀ” ገጽ በመሄድ ማመሳከር ያስፈልጋል። በስክሪን ቅጅው ላይ የሚነበበው መልዕክት በአቶ “ሀ” የፌስቡክ ገጽ ላይ ማግኘት ከተቻለ ትክክለኛ ነው ማለት ይቻላል። የስክሪን ቅጅዎ ከተባለው ገጽ ከሌለ ሀሠተኛ የመሆን ዕድል ሊኖረው ስለሚችል ተጨማሪ ማጣራቶችን ማድረግ ያስፈልጋል። 

በተጨማሪም በስክሪን ቅጅው ላይ የሚታዩ የፕሮፋይል ስምንና ምስል፣ ቀንና ሰዐት እንዲሁም የቋንቋ አጠቃቀም ስለቅጅው ትክክለኛነት ፍንጭ ሊሰጡን ስለሚችሉ በጥንቃቄ መመልከትያስፈልጋል። 

በማህበራዊ ትስስር ገጾች የምንመለከታቸውን  ስክሪን ቅጅዎች ከማመናችንና ለሌሎች ከማጋራታችን በፊት ትክክለኛ መሆናቸውን እናጣራ።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::