ይህ ምስል ሰሞኑን ትግራይ ክልል ውስጥ ሲንቀሳቀስ የነበረ የጦር ተሽከርካሪን ያሳያል?

ይህ ምስል ሰሞኑን ትግራይ ክልል ውስጥ ሲንቀሳቀስ የነበረ የጦር ተሽከርካሪን ያሳያል?

ሐምሌ 3፣ 2017

በርከት ያሉ የፌስቡክ ገጾች እና አካውንቶች በስክሪን ቅጂው ላይ የሚታየውን የጦር ተሽከርካሪ ምስል ከሰሞኑ በትግራይ ክልል እንደተነሳ በማስመሰል እያጋሩ መሆናቸውን ተመልክተናል።

የፌስቡክ ገጾቹ እና አካውንቶቹ ምስሉ “የህወሓት ጦር” ከሰሞኑ አደረገ ያሉትን እንቅስቃሴ የሚያሳይ እንደሆነ አመላክተዋል።

ይህን ምስል ካጋሩ ገጾች መካከል ከ300 ሺህ በላይ ተከታዮች ያሉት ‘Geez Media ግዕዝ ሚዲያ’ አንዱ ሲሆን “ከባድ መሳርያ አስረከበ የተባለው የህወሓት ጦር ዛሬ ዙ23 የታጠቀ ኦራል ይዘው ሲንጎራደዱ ውለዋል” የሚል ጽሁፍ ከምስሉ ጋር አጋርቷል።

በተጨማሪም ‘Tigray Military still has heavy wapons?’ በሚል ርዕስ መረጃ ያጋራው  የ‘My Views On News’ ዩትዩብ ቻነል አዘጋጅ ሳጂድ ነዲም “ምስሉን መርምሬዋለሁ፤ እናም አዲስ ምስል ነው” ብሏል።

ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ ቼክ በምስሉ ላይ ባደረገው ማጣራት በስክሪን ቅጂው የሚታየው የጦር ተሽከርካሪ ምስል ከሰሞኑ በትግራይ ክልል ውስጥ የተነሳ እንዳልሆነ አረጋግጧል።

ይህ ምስል ከቆየ ቪድዮ የተወሰደ ስክሪን ቅጂ (Screenshot) ሲሆን ባለፉት አመታት በተለያዩ ዩትዩብ ቻናሎች ተጋርቶ ነበር።

ምስሉ ስክሪንሻት የተደረገበትን ቪድዮ ከአመታት በፊት ካጋሩ ዩትዩብ ቻናሎች መካከል ‘ምቅናይ ዳኣ’ አንዱ ሲሆን ቻናሉ ቪድዮውን ከሶስት አመት በፊት እኤአ ሐምሌ 2021 ነበር ያጋራው፡ https://youtu.be/PLwtyalky-Y?si=nVCM-KF3y5FhS4Vy

ሰሞኑን ትግራይ ክልል ውስጥ እንደተነሳ ተደርጎ በተለያዩ ማህበራዊ ትስስር ገጾች እየተጋራ የሚገኘው የጦር መሳሪያ የጫነው ተሽከርካሪ ምስልም ከዚሁ ቪድዮ አምስተኛ ሴኮንድ ላይ ‘Screenshot’ የተደረገ መሆኑን ተመልክተናል።

ይሁንና ይህ ምስል የቆየ እንደሆነ በዚህ መልኩ ያረጋገጥን ቢሆንም የህወሀት ሀይሎች ከባድ መሳርያዎችን እና ብረት ለበስ ተሽከርካሪዎችን አሁን ድረስ ይዘው እንደሚገኙ አልፎ አልፎ በተለያዩ ስፍራዎች ላይ ይዘዋቸው እንደሚታዩ መረጃዎች ያሳያሉ።

የፕሪቶርያ ስምምነትን ተከትሎ ከባድ መሳርያዎችን ለኢትዮጵያ ጦር ሰራዊት ያስረከቡ ቢሆንም ዋናው የትጥቅ መፍታት ሂደት ቆሞ እንደሚገኝ መረጃዎች ያሳያሉ።

ከቆዩ ቪድዮዎች ስክሪን ቅጂ ተወስደው ከአውድ ውጭ የሚጋሩ ምስሎች ለሀሰተኛ እና የተሳሳተ መረጃ ሊያጋልጡን ስለሚችሉ ከማመናችን እና መልሰን ከማጋራታችን በፊት ተገቢዉን ማጣራት እናድርግ።

ኢትዮጵያ ቼክ!

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::