የስጋት መጠኑ እየጨመረ ስለመጣው የዝንጀሮ ፈንጣጣ በሽታ ምን ማወቅ አለብን?

የዝንጀሮ ፈንጣጣ (monkeypox) ቀዳሚ መገኛ ከሆኑት ምዕራብና መካከለኛው አፍሪካ ውጭ በተለይም በአውሮፓ፣ በሰሜን አሜሪካና በአውስትራሊያ ከተስፋፋ በኋላ የብዙዎች መነጋገሪያ ሆኗል።

የአሜሪካ የበሽታ መከላከያ እና መቆጣጠሪያ ማእከል (CDC) መረጃ እንደሚያሳየው እስከ ትናት ምሽት ድረስ በ29 ሀገሮች የዝንጀሮ ፈንጣጣ የተከሰተ ሲሆን 1,080 ሰዎች በበሽታው መያዛቸው ተረጋግጧል። ብሪታንያ፣ ስፔንና ፖርቱጋል ከፍ ያለ የበሽታው ተጠቂዎችን በማስመዝገብ ቀዳሚውን ቦታ ይዘዋል። አብዛኞቹ የበሽታው ተጠቂዎች የዝንጀሮ ፈንጣጣ ቀዳሚ መገኛ ወደሆኑት የምዕራብና የመካከለኛ አፍሪካ ሀገሮች የጉዞ ታሪክ የሌላቸው መሆኑንም መረጃዎች ያሳያሉ።

በሽታው በዝንጀሮ ፈንጣጣ ቫይረስ (monkeypox virus) አማካኝነት የሚከሰት ሲሆን ከእንስሳት ወደ ሰው እንዲሁም ከሰው ወደ ሰው የሚተላለፍ በሽታ መሆኑን የዓለም ጤና ድርጅት መረጃዎች ያሳያሉ። በሽታው ብዙውን ጊዜ በራሱ መዳን የሚችል ሲሆን የገዳይነት ምጣኔው እስከ 11% ሊደርስ ይችላል።

የዝንጀሮ ፈንጣጣ በበሽታው ከተያዘ እንስሳ ወይም ሰው ጋር በሚደረግ የቅርብ ንክኪ፣ ከሰውነት በሚወጣ ደም ወይም ፈሳሽ ጋር በሚኖር ንክኪ እንዲሁም በበሽታው የተጠቃን እንስሳን ተዋጽዎች በደንብ ሳያበስሉ በመመገብ ሊተላለፍ ይችላል።

በዝንጀሮ ፈንጣጣ የተያዘ ሰው ከ5 እስከ 21 ባሉት ቀናቶች ውስጥ ምልክቶችን ያሳያል። ራስ ምታት፣ ከፍ ያለ ትኩሳት፣ የዕጢዎች እብጠት፣ የጡንጃ ህመም እንዲሁም ድካም እና የቆዳ ሽፍታ የበሽታው ምልክቶች ናቸው።

የዝንጀሮ ፈንጣጣ ብዙውን ጊዜ በራሱ የሚድን ሲሆን ምልክቶችንና ተዛማች በሽታዎችን ማከም በህክምና ተቋማት የሚደረጉ ድጋፎች ናቸው። በበሽታው ከተያዙ እንስሳትና ሰዎች ጋር የሚኖር ንክኪ ላይ ጥንቃቄ ማድረግ የበሽታው ስርጭትን ለመከላከል በዋናነት ይጠቀሳል።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::