ኢትዮጵያ ውስጥ የተለያየ ቁስ ተገጥሞላት የተገኘችው ወፍ ምንድን ነች?
የካቲት 29፣ 2017
ከሰሞኑ በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ውስጥ የተለያዩ መለያዎች (tags) እና የመከታተያ ቁስ (tracking device) የተገጠመላት አንድ ወፍ መገኘቷ በሚድያዎች ተዘግቧል።
በክልሉ ማኦና ኮሞ ልዩ ወረዳ፣ ጉሬ ቀበሌ ውስጥ የተገኘችው ወፍ ጀርባ ላይ የተገጠመው ቁስ የብዙዎች መነጋገርያ ሆኗል። ጉዳዩን በክልሉ ከሚገኘው የህዳሴ ግድብ ጋር ያገናኙት እንዳሉ ሁሉ የተሸከመችው ቁስ ‘ምን ይሆን?’ የሚል ጥያቄ ያጫረባቸውም አሉ።
ለዚህም ይመስላል በራሪ እንስሳዋ በፀጥታ አካላት ተይዛ ለተጨማሪ ምርመራ ለመከላከያ ሰራዊት ተሰጥታለች።
ወፏ ጀርባ ላይ ‘ከተገኘች [email protected] በሚል ኢሜይል አሳውቁን’ የሚል መልዕክት ሲኖረው ኢትዮጵያ ቼክ በዚህ ዙርያ ዳሰሳ አድርጓል።
ዳሰሳው እንደሚጠቁመው በየአመቱ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ወፎች ባደጉ አገራት ባሉ አንዳንድ የአእዋፍ ጥናት በሚያደርጉ ተቋማት ለምርምር ስራ የተለያዩ መከታተያዎች ተገጥመውላቸው ይለቀቃሉ።
እነዚህ መከታተያዎች የGPS መሳርያ፣ የመለያ ቀለበት ወይም የታተመ ፅሁፍ ሊሆን እንደሚችል እና ጥናቱን የሚያደርጉት ሳይንቲስቶች የአእዋፉን የጉዞ አቅጣጫ፣ የቁጥር ብዛት፣ የእድሜ ርዝመት እና የበረራ መስመር ለማወቅ ይጠቀሙባቸዋል።
በወፎቹ ላይ የሚታየው ቁጥር የእያንዳንዱ በራሪ እንስሳ መለያ ሲሆን የተገጠመው ቁስ ደግሞ ወፎቹ በእያንዳንዱ የአየር መለዋወጥ ግዜ በየት አቅጣጫ በኩል እንደሚበሩ እንደሚመዘግብ ጥናቶች ያሳያሉ።
በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል የተገኘችውን ወፍ የለቀቀው በስዊድን ሀገር የሚገኘው BirdLife Sverige የተባለ ተቋም ሲሆን የአለም አቀፉ BirdLife International ድርጅት የስዊድን ቅርንጫፍ በመሆን እየሰራ ይገኛል።
እንዲህ አይነት አእዋፋት በኢትዮጵያ ሲከሰቱ የመጀመርያው አይደለም። የዛሬ አራት አመት ገደማ እንዲሁ አንድ አሞራ የተለያዩ ቀለበቶች ታስሮለት በኢትዮጵያ መገኘቱ በወቅቱ ተዘግቦ ነበር።
ኢትዮጵያ ቼክ
ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ
ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::