ንግድ ባንክ በመንግስት ብድር ዙርያ የሰጠው ማስተባበያ አሳሳች ነው
ሚያዚያ 1፣ 2017
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከትናንት በስቲያ በሰጠው መግለጫው ባንኩ “ለመንግስት አንድም ብር አበድሮ አያውቅም” በማለት አስታውቋል።
“የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በዚህ በጀት ዓመትም ሆነ ከዚያ በፊት አንድም ብር ለመንግስት በቀጥታ አበድሮ አያውቅም” ያለው ባንኩ መንግስት ከሀገር ውስጥ የንግድ ባንኮች፣ ማለትም በብሔራዊ ባንክ በኩል ለሽያጭ ከሚቀርበው የግምጃ ቤት ሰነድ ግዢ ውጪ በቀጥታ የመበደር አሰራርም ሆነ ልምድ የለውም ብሏል።
ባንኩ ማብራርያውን የሰጠው ሪፖርተር ጋዜጣ ባሳለፍነው እሁድ “መንግስት ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የተበደረው አንድ ትሪሊየን ብር እዳ እንዳለበት ተገለፀ” በሚል ለሰራው ዘገባ ነው።
ሪፖርተር በዘገባው ባንኩ የ2017 የበጀት አመት የስምንት ወራት የስራ አፈፃፀሙን ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ልማት ድርጅቶች ቋሚ ኮሚቴ ባቀረበበት ወቅት ባንኩ በአጠቃላይ ካለው የብድር ክምችት አንድ ትሪሊየን ብር እዳ የመንግስት መሆኑ መገለፁን ጠቅሷል።
ንግድ ባንክ ለዚህ የሰጠው ማስተባበያ ዋና መሰረት “የመንግስት የልማት ድርጅቶች ዕዳ መንግስት በቀጥታ ራሱ የተበደረው የመንግስት ዕዳ ሳይሆን የተለያዩ እንደ ባንካችን ያሉ የመንግስት የልማት ድርጅቶች የተበደሩት ዕዳ ነው” የሚል ነው።
ኢትዮጵያ ቼክ በዚህ ዙርያ አንድ የምጣኔ ባለሙያ እና ሌላ የባንክ ባለሙያ ያነጋገረ ሲሆን ሁለቱም የመንግስት የልማት ድርጅቶች እዳ የመንግስት እዳ መሆኑን ጠቅሰው የንግድ ባንክ ማስተባበያ ውሀ እንደማይቋጥር አስረድተዋል።
“ትርፍ ሲያተርፉ የመንግስት ተቋማት እንዳተረፉ የሚነገርላቸው፣ መንግስት የቦርድ አባላት የሚሾምላቸው እና መንግስት በአብዛኛው በባለከፍተኛ ድርሻነት የሚያንቀሳቅሳቸውን እነዚህ የልማት ድርጅቶች በብድር ጉዳይ ላይ ብቻ ለይቶ የመንግስት አይደሉም ማለት ትክክል አይደለም፣ አሳሳችም ነው” ያሉት የምጣኔ ባለሙያው የንግድ ባንክ መግለጫ ብዙ የኢኮኖሚ ባለሙያዎችን ግር እንዳሰኘ ለኢትዮጵያ ቼክ ጠቁመዋል።
የባንክ ባለሙያው በዚህ ተስማምተው “እነዚህ የልማት ድርጅቶች ሲያተርፉ መንግስት ይጠቀማል፣ ሲከስሩ ይጎዳል። የመንግስት የልማት ድርጅቶች የሚለው ከስያሜው ጀምሮ የሚያሳየው የመንግስት መሆናቸውን ነው” በማለት አስተያየታቸውን አጋርተዋል።
የባንክ ባለሙያው አክለውም በቅርቡ የልማት ድርጅቶችን የተከማቸ ብድር ለማቅለል በርካታ ቢልየን ብር ቦንድ ለህዝብ ለመሸጥ የታሰበው የመንግስት ተቋማት ስለሆኑ እንጂ የግል ቢሆኑ ይህን ማድረግ እንደማይታሰብ ጠቁመዋል።
በእነዚህ ሙያዊ አስተያየቶች ላይ ተመስርተን የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ያወጣው መግለጫ አሳሳች መሆኑን ለማየት ችለናል።
ኢትዮጵያ ቼክ!
ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ
ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::