ከህዳሴ ግድብ በቀን ከ14 ሺህ ቶን በላይ የአሳ ምርት የሚገኝበት አቅም ተፈጥሯል ተብሎ የተሰራጨው መረጃ ተጋኖ የቀረበ ነው
መጋቢት 18፣ 2017
በትናንትናው እለት የግብርና ሚኒስቴር ከታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በቀን ከ14 ሺህ ቶን በላይ የአሳ ምርት የሚገኝበት አቅም መፈጠሩን በሶሻል ሚድያ ገፁ አስታውቆ ነበር።
በግብርና ሚኒስቴር የአሳ ሀብት ልማት ዴስክ ሃላፊ ዶክተር ፋሲል ዳዊት በግድቡ በስፋት ተፈላጊ የሆኑ የአሳ ዝርያዎች እየተመረቱ መሆኑን ጠቅሰው በዚህም በቀን ከ14ሺህ 500 ቶን በላይ የአሳ ምርት የሚገኝበት አቅም መፈጠሩን አብራርተዋል።
ይሁንና ኢትዮጵያ ቼክ በዚህ ዙርያ ባደረገው ማጣራት መረጃው ተጋኖ የቀረበ መሆኑን ለመመልከት ችሏል።
14 ሺህ ቶን (ወይም 14 ሚልዮን ኪሎ ግራም) በአንድ ቀን ከህዳሴ ግድብ ብቻ ማምረት እንደሚቻል የቀረበው መረጃ የተሳሳተ መሆኑን ያገላበጥናቸው መረጃዎች ያሳያሉ።
ለአብነት ‘Fisheries and Aquatic Sciences’ የተባለው በአሳ ምርት ዙርያ ጥናት የሚያደርግ ተቋም ኢትዮጵያ ካሏት ግድቦች ማግኘት የምትችለው የአሳ ምርት መጠን ‘በአመት’ እስከ 8 ሺህ ቶን ሊደርስ እንደሚችል ይጠቁማል።
በሌላ በኩል Science Direct በመላው ኢትዮጵያ ካሉ የውሀ አካላት (ሀይቆች፣ ግድቦች፣ ወንዞች… ወዘተ) በአመት ሊገኝ የሚችለው የአሳ የምርት መጠን 94,500 ቶን እንደሆነ ይጠቁማል።
የግብርና ሚኒስቴር ይህን የትናንት የተሳሳተ መረጃውን በዛሬው እለት አስተካክሎ 14,500 ኪሎ ግራም እንዳለ የተመለከትን ቢሆንም የትናንት መረጃውን ይዘው የወጡ በርካታ ሚድያዎች እስካሁን 14,500 ቶን የሚል አሀዝ ይዘው እንደሚገኙ አስተውለናል።
የመንግስት የመረጃ ምንጮች ተደራሽነታቸው ሰፊ ስለሆነ በሚያቀርቧቸው ቁጥሮች እና መረጃዎች ላይ ጥንቃቄ ሊያደርጉ ይገባል፣ ስህተት ሲሰራ ደግሞ እርምት በግልፅ በማድረግ ህብረተሰቡን ማሳወቅ አለባቸው።
ኢትዮጵያ ቼክ
ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ
ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::