ፖፕ ፍራንሲስ ህይወታቸው እንዳለፈ ብሄራዊ ቴሌቭዥኑን ጨምሮ በአንዳንድ ሚድያዎች የተላለፈው ሀሰተኛ መረጃ እንዴት ተከሰተ?

ፖፕ ፍራንሲስ ህይወታቸው እንዳለፈ ብሄራዊ ቴሌቭዥኑን ጨምሮ በአንዳንድ ሚድያዎች የተላለፈው ሀሰተኛ መረጃ እንዴት ተከሰተ?

የካቲት 16፣ 2017

“የሮማ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንሲስ ከዚህ ዓለም ድካም አርፈዋል” በማለት የኢትዮጵያ ቴሌቭዥን ከጥቂት ሰአታት በፊት ያሰራጨው መረጃ የተሳሳተ ነበር።

ጣብያው ለምንጭነት የአለም አቀፉን የዜና ወኪል አሶሲየትድ ፕረስ (AP) በምንጭነት ዋቢ ቢያደርግም “Pope Francis rested during a peaceful night following respiratory crisis” ከሚለው አርዕስት ውስጥ ‘rested’ ወይም ‘እረፍት አደረጉ’ የሚለውን ‘ህይወታቸው አለፈ’ የሚል ትርጓሜ ሰጥቶት እንደነበር ኢትዮጵያ ቼክ ያደረገው ዳሰሳ እና ማጣራት ያሳያል።

በተመሳሳይ ድሬ ትዩብ የኢቢሲን ዘገባ ሳይጠቅስ ሊቀ ጳጳሱ እንዳረፉ አለም “አቀፍ ሚድያዎች እየዘገቡት ይገኛሉ” በማለት የተሳሳተ መረጃ አቅርቦ ነበር።

አሁን ላይ ሁለቱም ሚድያዎች ዜናዎቻቸውን አንስተዋል።

ኢቢቢ በሊቃነ ጳጳሱ ዙርያ የተሳሳተ ዜና ሰርቷል በማለት የኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ያስታወቀች ሲሆን “እንደውም ዛሬ ከበፊት ቀናት በተሻለ ሁኔታ ሰላማዊ እንቅልፍ ተኝተው ነው ያደሩት” በማለት ገልፃለች።

ፖፕ ፍራንሲስ የመተንፈሻ አካላቸው ላይ ጠንካራ ህመም ተከስቶባቸው ሆስፒታል ገብተው እንደሚገኙ አለም አቀፍ ሚድያዎች እየዘገቡ ይገኛሉ።

ሚድያዎች ሰበር ዜናዎችን ለማጋራት በሚጣደፉበት ግዜ እንዲህ አይነት የትርጉም እና የይዘት ግድፈት ሊያጋጥማቸው ስለሚችል ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባቸው ኢትዮጵያ ቼክ ለማሳሰብ ይወዳል።

ኢትዮጵያ ቼክ!

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::