“በዘንድሮው አመት ለኢትዮጵያ ምንም አይነት የውጭ እርዳታ አልተደረገላትም” የሚለው የኢቢሲ መረጃ ምን ያህል ትክክለኛ ነው?

የሚኒስትሮች ምክር ቤት በትናንትናው እለት የ10 ወራት አፈጻፀምን በተመለከተ ግምገማ አካሂዶ ነበር። በዚህ ወቅት በፕላን እና ልማት ሚኒስትር ዶ/ር ፍፁም አሰፋ አቅራቢነት በርካታ ዘርፎች ተዳስሰው ነበር።

ይህንን ግምገማ ተከትሎ ኢቢሲ በትናንትናው የቀትር ዜና ላይ “በዘንድሮው አመት ውስጥ ለኢትዮጵያ ምንም አይነት የውጭ እርዳታ አልተደረገላትም፣ ምንም አይነት እርዳታ ሳይደረግለት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ይህን ተሸክሞ መሄድ የቻለ መሆኑን ነው ሚኒስትሯ ባነሱት ሪፖርት ላይ መመልከት የቻልነው” የሚል መረጃ በጋዜጠኛው አማካኝነት አቅርቧል (https://www.youtube.com/watch?v=COnouab2c6I)

ኢትዮጵያ ቼክ በዚህ ዙርያ ዳሰሳ ያረገ ሲሆን ሚኒስትሯ ያቀረቡትን ሙሉ ሪፖርትም ተከታትሏል (https://fb.watch/duJiZuruw4/)

በሪፖርቱ ላይ እንደተቀመጠው የባለፈው አስር ወር የፌደራል መንግስት ገቢ 301.6 ቢልዮን ብር እንደሆነ ይጠቅስና ከዚህ ውስጥ 282.5 ቢልዮን ብር ከፌደራል ታክስ ገቢ እንዲሁም 19.1 የፌደራል ያልሆነ ታክስ ገቢ እንደሆነ ያስረዳል። ሪፖርቱ በዚሁ ወቅት የውጭ እርዳታ ገቢ ምንም እንዳልነበር ያስረዳል። ይህ ከላይ የተጠቀሰው የፌደራል በጀት ሲሆን በዚህ ወቅት ለቀጥተኛ የመንግስት በጀት ድጋፍ (direct budgetary assistance) ከውጭ ድጋፍ እንዳልተደረገ ያስረዳል። ለምሳሌ የአውሮፓ ህብረት ለኢትዮጵያ የሚያደርገውን የ107 ሚልዮን ዶላር ቀጥተኛ የበጀት ድጋፍ ከሰሜኑ ጦርነት ጋር በተያያዘ አምና መያዙን አሳውቆ ነበር።

ይሁንና በዚህ ወቅት ቀጥተኛ ያልሆኑ በርካታ ድጋፎች ለኢትዮጵያ ተደርገው ነበር። ለምሳሌ የአለም ባንክ በግጭት የተጎዱ ዜጎችን ለመደገፍ የ300 ሚልዮን ዶላር ድጋፍ የዛሬ ሁለት ወር ገደማ አድርጎ ነበር። በዛሬው እለትም የዓለም ባንክ በኢትዮጵያ የከርሰ ምድር ውሃ በብዛት በሚገኝባቸው ዝናብ አጠር እና ቆላማ አካባቢዎች የከርሰ ምድር ውሃን ለማልማት እና ጥቅም ላይ ለማዋል የሚያስችል የ210 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ድጋፍ አድርጓል።

ስለዚህ “በዘንድሮው አመት ውስጥ ምንም አይነት የውጭ እርዳታ ለኢትዮጵያ አልተደረገላትም” በሚል በኢቢሲ የቀረበው መረጃ አሳሳች ሲሆን ትክክለኛው መረጃ “ለፌደራል በጀት የውጭ የበጀት ድጋፍ በተባለው ግዜ ውስጥ ምንም አልተደረገም” የሚለው መሆኑን ማየት እንችላለን።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::