የታዋቂውን ሲኒማቶግራፈርና ዳይሬክተር ሰውመሆን ይስማውን (ሶሚክ) ስምና ፎቶ በመጠቀም የተከፈተ ሀሠተኛ የፌስቡክ አካውንት
መስከረም 20፣ 2017 ዓ.ም
የታዋቂው ሲኒማቶግራፈርና ዳይሬክተር ሰውመሆን ይስማውን (ሶሚክ) ስምና ፎቶ በመጠቀም የተከፈተ የፌስቡክ አካውንት መኖሩን ተመልክተናል።
ይህ ‘Sewmehon Yismaw’ የሚል ስም የሚጠቀም አካውንት ለፍቅር እስከመቃብር ተከታታይ ፊልም ላይ የሚሳተፉ አዳዲስ አጃቢና ረዳት ተዋንያንን እንፈልጋለን የሚል ማስታወቂያ በማስነገር ላይ መሆኑንም አስተውለናል።
“ከአሁን በፊት ምንም ስራ ላይ ያልተሳተፉ አዳዲስ ተዋንያን” ብቻ እንደሚፈልጉ የሚያስነግረው ይህ አካውንት ፍላጎት ያላቸው ተመዝጋቢዎች ፎቶ እና አጭር ቪዲዮ በቴሌግራም እንዲልኩ ይጠይቃል። በርካታ ሰዎችም እውነት እንደመሰላቸው ተረድተናል።
ጉዳዩን በተመለከተ ኢትዮጵያ ቼክ ሰውመሆን ይስማውን ያነጋገረ ሲሆን ከላይ የተጠቀሰው የፌስቡክ አካውንት የእርሱ አለመሆኑንና የተጋራው መረጃም ሀሠተኛ መሆኑን አስታውቋል።
ይህ ሀሠተኛ አካውንት በሚያጋራቸው የተሳሳቱ መረጃዎች መቸገሩን የገለጸው ሰውመሆን ምንም አይነት የተዋናይ ምልመላ አለመጥራታቸውንና በቴሌግራም የሚላኩ ፎቶዎችና ቪዲዮዎችም ወደእነርሱ የሚደርሱ አለመሆናቸውን ተናግሯል።
የሰውመሆን ይስማው ትክክለኛ የፌስቡክ አካውንት የሚከተለውን ማስፈንጠሪያ በመከተል ማግኘት ይቻላል: https://www.facebook.com/somickk
ተመሳስለው የተከፈቱ ሀሰተኛ አካውንቶችን ባለመከተል ከሀሰተኛና ከተዛቡ መረጃዎችን ስርጭት እራሳችንን እንጠብቅ!
ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ
ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::