ፌስቡክ በኢትዮጵያ በሚነገሩ ቋንቋዎች የሚስተጋቡ የጥላቻ ንግግሮችን የመለየት አቅሙን ለመፈተሽ ፈትኜው በተደጋጋሚ ወድቋልሲል ግሎባል ዊትነስ የተባለ ተቋም አስታወቀ።

“ፌስቡክ በኢትዮጵያ በሚነገሩ ቋንቋዎች የሚስተጋቡ የጥላቻ ንግግሮችን የመለየት አቅሙን ለመፈተሽ ፈትኜው በተደጋጋሚ ወድቋል”— ግሎባል ዊትነስ

– “እንዲስተጋቡ የተጠየቁት መልዕክቶች ከኛ ፖሊሲ ጋር የሚቃረኑ ናቸው፣ ሆኖም ለፌስቡክ ተጠቃሚዎች ከመድረሳቸው በፊት እንዲሰረዙ ተደርገዋል’’— ፌስቡክ ለኢትዮጵያ ቼክ

“ፌስቡክ በኢትዮጵያ በሚነገሩ ቋንቋዎች የሚስተጋቡ የጥላቻ ንግግሮችን የመለየት አቅሙን ለመፈተሽ ፈትኜው በተደጋጋሚ ወድቋል” ሲል ግሎባል ዊትነስ የተባለ ተቋም በትናንትናው እለት አስታውቋል።

ግሎባል ዊትነስ ይፋ ባደረገው ሪፖርት ፌስቡክን ለመፈተን ያዘጋጃቸው የጥላቻ መልዕክቶች በክፍያ እንዲስተጋቡለት (ads) መጠየቁን የገለጸ ሲሆን መልዕክቶቹም እንዲስተጋቡ ፌስቡክ መፍቀዱን አስታውቋል።

ግሎባል ዊትነስ በፌስቡክ እንዲስተጋቡለት ክፍያ የፈጸመባቸው በአማርኛ ቋንቋ የተጻፉ 12 የጥላቻ መልዕክቶች ሲሆኑ መልዕክቶቹ ከዚህ ቀደም በሌሎች የፌስቡክ ተጠቃሚዎች የተጋሩ ነበሩ። እነዚህ የጥላቻ መልዕክቶች በአማራ፣ በኦሮሞ እና በትግራይ ብሄሮች ላይ በእኩል ያነጣጠሩ ነበሩ ያለው ተቋሙ ከዚህ ቀደም ሪፖርት ተደርገው የተወሰኑት በፌስቡክ እርምጃ የተወሰደባቸው መሆኑን አስታውሷል።

ፌስቡክን ለመፈተን የተመረጡት 12ቱ የጥላቻ መልዕክቶች የከፉ፣ ቀጥተኛና የማያሻሙ እንዲሁም ፌስቡክ ራሱ ካወጣቸው ፖሊሲዎች ጋር የሚጣራሱ መሆናቸውን የገለጸው ግሎባል ዊትነስ ሆኖም 12ቱም የጥላቻ መልዕክቶች በክፍያ እንዲስተጋቡ መፈቀዱንና በዚህም ፌስቡክ ፈተናውን መውደቁን በሪፖርቱ ይፋ አድርጓል።

ለፈተና የተመረጡት የጥላቻ መልዕክቶች እንዲስተጋቡ ከፍያ ቢፈጸምባቸውም በቀነ-ቀጠሮ የተያዙ ረቂቆች ስለነበሩ አለመጋራታቸውን ግሎባል ዊትነስ ጨምሮ ገልጿል።

ግሎባል ዊትነስ ከፈተናው በኋላ የአሰራር ግድፈቶቹን ለፌስቡክ ማስታወቁን፣ ፌስቡክም ስህተቱን ማመኑን በሪፖርቱ አስነብቧል። ነገር ግን ከሳምንት በኋላ ተጨማሪ ሁለት በአማርኛ ቋንቋ የተዘጋጁና ከነባራዊው ዓለም የተቀዱ የጥላቻ መልዕክቶች በክፍያ እንዲስተጋቡለት ለፌስቡክ ጥያቄ አቅርቦ በሰዐታት ውስጥ ይሁንታ ማግኘቱን ተቋሙ አስታውቋል።

ይህም ፌስቡክ ፈተናውን በድጋሜ መውደቁንና በኢትዮጵያ ቋንቋዎች የሚሰራጩ የጥላቻ መልዕክቶችን በመለየት ረገድ ያለበትን ትልቅ ክፍተት ያሳያል ብሏል።

ኢትዮጵያ ቼክ ፌስቡክ ፈተናዎቹን ወድቋል መባሉን በተመለከተ የማህበራዊ መገናኛ ዘዴውን ማብራሪያ ጠይቋል።

የፌስቡክ እናት ድርጅት የሆነው ሜታ ለኢትዮጵያ ቼክ በሰጠው ማብራሪያ “ግሎባል ዊትነስ” እንዲስተጋቡለት ክፍያ የፈጸመባቸው መልዕክቶች በርግጥም የፌስቡክን ፖሊሲ የጣሱ እንደነበሩ አምኗል። “እንዲስተጋቡ የተጠየቁት መልዕክቶች ከኛ ፖሊሲ ጋር የሚቃረኑ ናቸው፤ ሆኖም ለፌስቡክ ተጠቃሚዎች ከመድረሰቸው በፊት እንዲሰረዙ ተደርገዋል’’ በማለት ምላሽ የሰጠው ሜታ መልዕክቶቹ የተሰረዙት እራሱ በወሰደው እርምጃ ወይም “በግሎባል ዊትነስ” ስለመሆኑ አልገለጸም።

ሜታ ኢትዮጵያን በተመለከት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ለኢትዮጵያ ቼክ በሰጠው ማብራሪያ ገልጾ፤ ተጨማሪ ኢትዮጵያውያን ባለሙያዎችን መቅጠሩን እንዲሁም አማርኛን ጨምሮ በስፋት በሚነገሩ ቋንቋዎች የሚሰራጩ የጥላቻና ሁከት ቀስቃሽ መልዕክቶችን ለመለየት የአቅም ግንባታ ስራዎችን መከወኑን በምሳሌነት አንስቷል።

ሜታ ከላይ የተጠቀሱት ስራዎች እየሰራ መሆኑን ያስረዳ ቢሆንም ማሽኖችም ሆነ ሰዎች ስህተት ሊሰሩ እንደሚችሉ በሰጠው ማብራሪያ አስታውሷል። “ምንም እንኳን ትኩረት ሰጥተን ብንቀሳቀስም ሁሌም የምንስታቸው በምሳሌነት የሚጠቀሱ ነገሮች ይኖራሉ፤ በስህተት የምንሰርዛቸው መልዕክቶችም አይጠፉም” በማለት አብራርቷል።

ፌስቡክ በኢትዮጵያ ቋንቋዎች የሚሰራጩ የጥላቻ መልዕክቶችን እንዲሁም የሠተኛና የተዛቡ መረጃዎችን ስርጭት በመቆጣጠር እረገድ ከፍተኛ ድክመት እንዳለበት የተለያዩ ወገኖች ከዚህ በፊት በተደጋጋሚ መግለጻቸው ይታወሳል።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::