እነዚህ ምስሎች የኢትዮጵያ አየር መንገድ በቢሾፍቱ ከተማ የሚያስገነባው ሜጋ ኤርፖርት ፕሮጀክትን ያሳያሉ?

Do these images show the mega airport project that Ethiopian Airlines is building in Bishoftu city?

ሕዳር 21፣ 2017 ዓ.ም

ከሰሞኑ በርከት ያሉ የፌስቡክ እና ኤክስ (ትዊተር) ተጠቃሚዎች የኢትዮጵያ አየር መንገድ በቢሾፍቱ ከተማ የሚያስገነባውን ሜጋ ኤርፖርት ፕሮጀክት ያሳያሉ ያሏቸውን ምስሎች እያጋሩ ይገኛሉ።

ለምሳሌም ‘FastMereja.com’ የሚል ስም ያለው እና ከ860 ሺህ በላይ ተከታዮች ያሉት የፌስቡክ ገጽ “የኢትዮጵያ አየር መንገድ በ5 ቢሊየን ፓውንድ በቢሾፍቱ ከተማ የሚገነባው “ሜጋ ኤርፖርት ከተማ” ፕሮጀክት ይፋ ተደረገ” ሲል በስክሪን ቅጂው የሚታዩትን ሶስት ምስሎች አጋርቷል።

ይህን የፋስት መረጃ ልጥፍም ከ40 በላይ የፌስቡክ ተጠቃሚዎች መልሰው አጋርተውታል።

ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ ቼክ የጉግል ምስልን በምልሰት መፈለጊያን በመጠቀም በምስሎቹ ላይ ባደረገው ማጣራት በስክሪን ቅጂው የታችኛው ክፍል የሚታዩት ሁለት የኤርፖርት ንድፎች በደቡብ ኮሪያ የሚገኘው የኢንቾን ኤርፖርት ንድፍ መሆናቸውን ማረጋገጥ ችሏል።
የኢንቾን ኤርፖርት ንድፎች በተለያዩ ጊዝያት ሲጋሩ የቆዩ ሲሆን ከንድፎቹ የተወሰኑትን በነዚህ ማስፈንጠሪያዎች መመልከት ይቻላል፡ https://www.gensler.com/projects/incheon-international-airport እና https://www.koreaherald.com/view.php?ud=20191119000078

በሌላ በኩል በስክሪን ቅጂው የላይኛው ክፍል የሚገኘው ምስል ‘GSAAN’ በተሰኘ ድረ-ገጽ የተጋራ ሲሆን ተቋሙ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለሚገነባው ሜጋ ኤርፖርት የቅድም ዲዛይን እና ማስተር ፕላን ጽንሰ-ሐሳብ አገልግሎት መስጠቱን ጠቅሷል፡https://www.gsaan.us/ethiopia-new-airport-logistics-industry-park-project-study-report/

ይሁን እንጂ ‘GSAAN’ ድረ-ገጽ ላይ የተጋራውን ንድፍ ከሌላ ምንጮች ማረጋገጥ አልቻልንም።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በበኩሉ በቢሾፍቱ ከተማ ለሚያስገነባው ሜጋ ኤርፖርት ከዳር አል ሀንዳሽ የግንባታ አማካሪ ድርጅት ጋር የቴክኒካል፣ የአርክቴክቸር፣ የኢንጅነሪንግ እና ፕሮጀክት ማኔጅመንት ስምምነት መፈራረሙን ባለፈው ነሐሴ 2016 በድረ-ገጹ ባጋራው መግለጫ አስታውቆ ነበር፡ https://corporate.ethiopianairlines.com/Press-release-open-page/ethiopian-airlines-signs-a-contract-with-dar-al-handasah-to-develop-a-mega-airport-city

በተጨማሪም ኢትዮጵያ ቼክ ባደረገው ማጣራት በኢትዮጵያ አየር መንገድም ሆነ በዳር አል ሀንዳሽ የግንባታ አማካሪ ድርጅት ይፋ የሆነ የሜጋ ኤርፖርቱ ንድፍ እንደሌለ ተመልክተናል።

በሌላ በኩል ከአዲስ አበባ ቦሌ አለም አቀፍ ኤርፖርት በ40 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ እንደሚገነባ የተነገረው ሜጋ ኤርፖርት በአመት 110 ሚሊዮን መንገደኞችን የማስተናገድ አቅም እንዳለው ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ድረ-ገጽ ያገኘነው መረጃ ይጠቁማል።

ኢትዮጵያ ቼክ

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::