መጪው ትልቁ ፈተናችን: የሀሰተኛ መረጃ ስርጭት!

ስለፒዛጌት ሰምታችሁ ይሆናል። እአአ በ2016 የአሜሪካ ፕሬዝደንታዊ ምርጫ ወቅት ሶሻል ሚድያ ላይ “ኮሜት” የተባለ የፒዛ መሸጫ ቤት ውስጥ የዴሞክራቲክ እጩ የነበሩት ሂላሪ ሮድሀም ክሊንተን ህፃናትን የሚያሰቃዩበት ክፍል አላቸው ተብሎ ተወራ።

የፒዛ ቤቱ ባለቤት ጄምስ አለፋንቲስ “መጀመርያ የምርጫ ሰሞን ጫጫታ ነው፣ ውሸት ስለሆነ ጊዜው ሲሄድ አብሮ ይረሳል ብዬ አስቤ ነበር” ይላል። እውነታው ግን በተቃራኒው ነበር። ይህ የሀሰት መረጃ በፌስቡክ፣ ትዊተር፣ ሬዲት እንዲሁም አሌክስ ጆንስ በተባለ ቀኝ-ዘመም አክራሪ ግለሰብ አማካኝነት ከአሜሪካ አልፎ አለምን አዳረሰ።

በዚህ ግዜ የአሜሪካ የደህንነት አባላት የፒዛ መሸጫ ውስጥ ገብተው ሲፈትሹ ምንም ነገር እንደሌለ ይገነዘባሉ። ይህንን ለህዝቡ ቢያስረዱም ብዙ ሰው ግን ቀድሞ እውነት ነው ብሎ ስላመነ ለመቀበል ፈቃደኛ አልነበረም።

ከዚያ የፒዛ ቤቱ ባለቤቶች አበሳ ይጀምራል። “ኮሜት” የህፃናት ማሰቃያ ቦታ ነው ስለተባለ ገበያ ቀዘቀዘ፣ ሰራተኞቹ የሞት ማስፈራርያ በየቀኑ ይደርሳቸው ጀመር፣ በሁዋላም ከባድ መሳርያ የታጠቀ ሰው ሰተት ብሎ ገብቶ ፍተሻ ሲያደርግ በፖሊስ ተይዟል።

የዚህ ሁሉ መነሻ ግን በሶሻል ሚድያ እና አሌክስ ጆንስ በተባለ የሬድዮ ፕሮግራም አዘጋጅ የተነዛ የሀሰት መረጃ ነበር።

በሀገራችንም የሀሰተኛ መረጃ ከአክቲቪስት እስከ ሚድያ ባለሙያ፣ ከመንግስት ሀላፊ እስከ ተቃዋሚ፣ ከቡድኖች እስከ ማህበሮች ወዘተ ጭምር እየተሰራጨ ነው። ሀይ ባይ ያጣው ሶሻል ሚድያ የፈለጉትን የሚሳደቡበት፣ በሀሰት የሚወነጅሉበት፣ ስም የሚያጠፉበት እንዲሁም ሰውን ለጥቃት የሚያነሳሱበት እየሆነ ነው።

ወደፊት የሚያስፈራው በሶሻል ሚድያ በሚወጡ የሀሰት መረጃዎች ከፒዛጌት ከበድ ያሉ ችግሮች እንዳይፈጠሩ ነው። ለዚህም ሁላችንም ለሀሰተኛ መረጃ ጆሮ አለመስጠት እና ሲገኝም ማጋለጥ ይኖርብናል።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::