ጠ/ሚር አብይ አህመድ እንደፃፉት ተደርጎ ዛሬ እየተሰራጨ የሚገኘው ደብዳቤ ሀሰተኛ ነው!
መጋቢት 27፣ 2017
በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ለአቶ ጌታቸው ረዳ በዛሬው እለት ማለትም መጋቢት 27/2017 ዓ/ም እንደተፃፈ ተደርጎ እየተሰራጨ የሚገኝ ደብዳቤ እንዳለ ተመልክተናል።
“የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ርዕሰ መስተዳድር ሆነው እንዲቀጥሉ” በሚል ርዕስ ተቀናብሮ የቀረበው ደብዳቤው አቶ ጌታቸው ረዳ የክልሉ ግዜያዊ አስተዳደር ሆነው እንዲቀጥሉ በጠቅላይ ሚኒስትሩ መወሰኑን ይገልፃል።
ኢትዮጵያ ቼክ በደብዳቤው ላይ ባደረገው ማጣራት በቅንብር የቀረበ ሀሰተኛ ደብዳቤ መሆኑን አረጋግጧል።
ሀሰተኛ ደብዳቤው መጋቢት 13/2017 ዓ/ም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለረዳት ፕ/ር ነብዩ ባዬ የሰጡትን ትክክለኛ ደብዳቤ በመጠቀም እና እሱን ኤዲት በማድረግ የተቀናበረ መሆኑን ለማየት ችለናል።
ከዚህም በተጨማሪ ፎቶፎረንሲክስ በመጠቀም ባደረግነው ማጣራት ‘መጋቢት 27’ የሚለው ቀን እና ሙሉው የደብዳቤው የፅሁፍ አካል በቅንብር ተቆርጦ ለረዳት ፕ/ር ነብዩ የተፃፈው ደብዳቤ ላይ መቀጠሉን አይተናል።
አቶ ጌታቸው ረዳ ዱባይ ላይ ከአንድ ሚድያ ጋር ትናንት ባደረጉት ቃለመጠይቅ አሁንም ከስራ ጋር የተያያዘ ፊርማ እየፈረሙ እንደሆነ ጠቅሰው ገለል እንዲሉ የተፈለገው “ከቀደምት ታጋይ ፖለቲከኞች መሀል አንዱ ስላልሆንኩ ነው” ብለው ተናግረዋል።
ጠ/ሚሩ ቀጣዩን የክልሉን ጊዜያዊ አስተዳደር መሪ ለመምረጥ ህዝቡ በኢሜይል ጥቆማ እንዲሰጥ ከቀናት በፊት ሀሳብ ቢያቀርቡም ይህ አካሄድ በዶ/ር ደብረፅዮን ገ/ሚካኤል በሚመራው የህወሀት ቡድን በኩል ጥብቅ ተቃውሞ እንደገጠመው ይታወሳል።
ኢትዮጵያ ቼክ!
ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ
ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::