የኢንዱስትሪ ሚንስትሩን የአቶ መላኩ አለበልን ስምና ምስል በመጠቀም የተከፈተ ሀሰተኛ የፌስቡክ አካውንት
ነሐሴ 2፣ 2016 ዓ.ም
የኢንዱስትሪ ሚንስትሩን የአቶ መላኩ አለበልን ስምና ምስል በመጠቀም የተከፈተ የፌስቡክ አካውንት የገንዘብ ድጋፍ (grant) የሚያስገኝ ውድድርን የተመለከተ መልዕክት እያጋራ እንደሆነ ተመልክተናል።
ይህ ‘H.E. Meleku Alebel’ የሚል ስያሜን የሚጠቀም የፌስቡክ አካውንት የገንዘብ ድጋፉን የተመለከቱ መልዕክቶችን ለፌስቡክ ክፍያ በመፈፀም (promote/sponsor በማድረግ) እንደሚያስተጋባም አስተውለናል።
በገጹ የሚጋሩ የገንዘብ ድጋፍ የሚያስገኙ ውድድሮችም በርካታ ገንዘብ የሚያስገኙ መሆናቸው የሚነበብ ሲሆን በአቀራረብም ትክክለኛ እንዲመስሉ ሆነው የተዘጋጁ ናቸው።
ሆኖም የኢንዱስትሪ ሚንቴር ገጹም ሆነ በገጹ የሚጋሩ የገንዘብ ድጋፍ ውድድሮች ሀሠተኛ መሆናቸውን አስታውቋል።
ከዚህ ቀደምም ‘Mr Melaku Alebel’ የሚል ስያሜ የሚጠቀም የፌስቡክ ገጽ ተመሳሳይ መልዕክቶችን ስፖንሰር በማድረግ ሲያሰራጭ የነበረ ሲሆን በኢትዮጵያ ቼክ መጋለጡ ይታወሳል። አቶ መላኩ አለበል በኤክስ ትዊተር ማረጋገጫ ያለው አካውንት እንዳላቸው ነገር ግን የፌስቡክ ገጽ እንደሌላቸው ሚንስቴር መስሪያ ቤቱ በወቅቱ ለኢትዮጵያ ቼክ አስታቆም ነበር።
ተመሳስለው የተከፈቱ ሀሰተኛ ገጾችን እና አካውንቶችን ባለመከተል ከሀሰተኛና ከተዛቡ መረጃዎችን ስርጭት እራሳችንን እንጠብቅ!
ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ
ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::