በትግራይ ክልል ውስጥ በሚገኙ የኤርትራ የስደተኞች ካምፖች ውስጥ ያሉ ሰዎች ምን እያጋጠማቸው ነው?

በትግራይ ክልል ውስጥ በሚገኙ የኤርትራ የስደተኞች ካምፖች ውስጥ ያሉ ሰዎች ምን እያጋጠማቸው ነው?

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መረጃ ማጣሪያ በትናንትናው እለት ባወጣው መግለጫ የኢትዮጵያ መንግስት በትግራይ ክልል ካሉ የኤርትራውያን የስደተኞች ካምፖች ወጥተው ወደ አዲስ አበባ የገቡ የኤርትራ ስደተኞችን ወደ መጡበት መመለስ መጀመሩን ገልጿል፣ ይህም ስደተኞቹ አስፈላጊውን እርዳታ እንዲያገኙ ያስችላል ብሏል።
የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች መርጃ ድርጅት (UNHCR) በበኩሉ በትናንትናው እለት ባወጣው መግለጫ ግጭቱ ከተነሳ ጊዜ ጀምሮ ትግራይ ክልል ውስጥ ወደሚገኙ አራት የኤርትራውያን የስደተኛ ካምፖች መድረስ እንዳልቻለ እና ግንኙነቶች መቋረጣቸውን፣ ይህም የስደተኞቹን ደህንነት እንደሚጎዳ ገልጿል።
ካለፈው አንድ ወር ወዲህ እነዚህ ኤርትራውያን ስደተኞች የሞት፣ ታፍኖ የመሰወር እንዲሁም በሀይል ወደ ኤርትራ የመወሰድ እጣ ፈንታ እንደደረሰባቸው የሚጠቁሙ “የሚረብሹ” ሪፖርቶች እንደደረሳቸው የድርጅቱ የድርጅቱ ኮሚሽነር ፊሊፖ ግራንዲ ተናግረዋል፣ ይህም እውነታው ከተረጋገጠ ትልቅ የአለም አቀፍ ህግ ጥሰት ይሆናል ብለዋል፣ ስደተኞችንም ወደተሰደዱበት ሃገር ያለፍላጎታቸው መመለስ በጭራሽ ተቀባይነት የለውም ሲሉ ተሰምተዋል።
በሌላ በኩል የአለም የስደተኞች ጉዳይ ድርጅት (IOM) በትናንት መግለጫው ድርጅቱ የኤርትራ ስደተኞችን አግቶ በመያዝ ወደ ኤርትራ ለመመለስ አዲስ አበባ በሚገኘው የትራንዚት ቢሮው እንዳስቀመጣቸው ተደርጎ የሚሰራጨው ዜና “ውሸት” እንደሆነና በድርጅቱ መኪናዎች ስደተኞችን ወደማይታወቅ ቦታ እንደወሰዷቸው የሚነገረው “ሀሰት” መሆኑን እወቁት ብሏል።
ድርጅቱ አክሎ እንደገለፀው አዲስ አበባ የሚገኘው አንዱ ቢሮው በስደተኞችና ከስደት ተመላሾች ጉዳይ ኤጀንሲ ከጥቅምት 24 ጀምሮ እንደተወሰደ ገልጿል።
Photo: NCPS

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::