ከቁጥጥር ውጭ ሆኗል የተባለው የቻይና ሮኬት ኢትዮጵያን ጨምሮ አንዳንድ የአፍሪካ ሀገራትን ሊመታ ይችላል? 

በሽር ሀሺ ዩሱፍ የተባለ እና ከ27,000 በላይ የትዊተር ተከታይ ያለው ግለሰብ ሰሞኑን ከቁጥጥር ውጭ ሆኗል የተባለው Long March 5B የቻይና ሮኬት ኢትዮጵያን ጨምሮ አንዳንድ የአፍሪካ ሀገራትን በመጪው ቅዳሜ ሊመታ ይችላል የሚል መረጃ በትናንትናው እለት አጋርቷል፣ መረጃውም በብዙ ሰዎች ዘንድ ግብረ-መልስ አግኝቷል እንዲሁም ተጋርቷል። 

ኢትዮጵያ ቼክ በዚህ ዙርያ አለም አቀፍ ሚድያዎች የሰሯቸውን የተለያዩ ዘገባዎች የተመለከተ ሲሆን ይህም እንደሚከተለው ይቀርባል። 

ሲኤንኤን:

ጆናታን ማክዶዌል የተባሉ የጠፈር ተመራማሪ ለሲኤንኤን እንደተናገሩት ሮኬቱ እዚህ ወይም እዛ ጋር ይወድቃል ብለው ለሚናገሩ ሰዎች ጆሮ መስጠት እንደማያስፈልግ ይናገራሉ። ተመራማሪው አክለውም ጉዳዩ ጭራሽ የሚያሳስብ እንዳልሆነ አስረድተው “የሮኬቱ ፍርስራሽ የት ሊወድቅ እንደሚችል ከአሁኑ መገመት አይቻልም፣ ቢያንስ ወደ ምድር ሲቃረብ ይቀላል። ይህም ሆኖ መዳረሻው ውቅያኖስ ላይ ሊሆን መገመት ይሻላል ምክንያቱም የመሬት አብዛኛው ክፍል በውሀ የተሸፈነ ስለሆነ” ብለዋል። 

ዘ-ጋርዲያን:

ዘ-ጋርዲያን ኤሮስፔስ የተባለ ድርጅትን ጠቅሶ እንደፃፈው የሮኬቱ አካል ምስራቃዊ የአሜሪካ ከተሞችን ካለፈ በሗላ በፓስፊክ የምድር ወገብ አካባቢ ይወድቃል ተብሎ እንደሚጠበቅ ዘግቧል። የአሜሪካ መከላከያ መስሪያ ቤት ይህ የሮኬት አካል ቅዳሜ ወደ ምድር ይደርሳል ብሎ እንደገመተም ይህ ሚድያ አስነብቧል። 

ዋሽንግተን ፖስት:

ይህ ሚድያ ደግሞ የቻይና የመንግስት ሚድያዎችን ጠቅሶ እንደፃፈው “የሮኬቱ የውጭ አካል በቀጭን የአልሙኒየም ብረት የተሸፈነ ስለሆነ ህዋ ላይ በቀላሉ ይቃጠላል፣ ይህም ሰዎች ላይ ሊደርስ የሚችል አደጋን እጅግ፣ እጅግ አናሳ ያደርገዋል።” 

እነዚህ እና ሌሎች ሪፖርቶች እንደሚያመለክቱት በሽር ሀሺ ዩሱፍ ያጋራው መረጃ ምንጩ የማይታወቅ ብቻ ሳይሆን ሌላ የትም ቦታ ያልተዘገበ መሆኑን ነው፣ ትልልቅ አለም አቀፍ ሚድያዎች ደግሞ ለእንዲህ አይነት መረጃዎች ከግለሰቦች ይልቅ ሰፋ ያሉ ምንጮች እንዳሏቸው ይታወቃል። 

በዚህም መሰረት ኢትዮጵያ ቼክ ይህን መረጃ ቅይጥ (ግማሽ እውነት፣ ግማሽ ሀሰት) ሆኖ አግኝቶታል። የሮኬቱ ከቁጥጥር ውጭ መሆን ትክክለኛ መረጃ ሲሆን አንዳንድ የአፍሪካ ሀገራትን ሊመታ ይችላል የሚለው ግን ትክክለኛ እንዳልሆነ መረዳት ይቻላል።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::