ዛሬ በአዲስ አበባ ተከስቶ ለነበረው እና “ታይቶ የማይታወቅ” ለተባለው የትራፊክ መጨናነቅ ምክንያቱ ምን ነበር?

በዛሬው እለት አንዳንድ የአዲስ አበባ አካባቢዎች “ታይቶ የማይታወቅ” የተባለ የትራፊክ መጨናነቅ አጋጥሟቸው ነበር። እጅግ ባልተለመደ መልኩ እስከ ሶስት ሰአት ያህል መኪና ውስጥ ሆነው መንቀሳቀስ ያቃታቸው ሰዎች እንደነበሩ ለኢትዮጵያ ቼክ የደረሰው ጥቆማ ያመለክታል።

በተለይ ከአዋሬ አደባባይ እስከ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲሁም ከ22 እስከ ኡራኤል ቤተክርስቲያን ያሉት መንገዶች እጅጉን ተዘጋግተው እንደነበር ታውቋል።

ኢትዮጵያ ቼክ ባደረገው ማጣራት ምክንያቱ የአዲስ አበባ ብልፅግና ፓርቲ ከተማ አቀፍ የምርጫ ቅስቀሳ መርሐግብር እያካሄደ የተፈጠረ መሆኑን ነው። መንግስታዊው ሚድያ ኢብኮ እንደዘገበው በበርካታ ተሽከርካሪዎች በመታጀብ የምርጫ ቅስቀሳው ዛሬ የተደረገ ሲሆን በፕሮግራሙ ላይ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና ለአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት ብልጽግና ፓርቲን ወክለው የሚወዳደሩ እጩዎች ተሳትፈዋል።

በርካቶችን ዛሬ ለእንግልት ዳርጎ በነበረው በዚህ የምርጫ ቅስቀሳ ዙርያ ብዙ አስተያየቶች ተሰጥተዋል፣ አንዳንዶች የሳምንት ማብቂያ (እሁድ) ላይ ቢደረግ ጥሩ እንደነበር ሲገልፁ ሌሎች ደግሞ መሀል ከተማ መንገድ ተዘግቶ ቅስቀሳው መደረጉ ትክክል እንዳልሆነ ፅፈዋል።

በዚህ ዙርያ የእርስዎን አስተያየት ያጋሩን።

Photo Credit: AA City Press Secretariat/Driving in Addis

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::