ባህርዳር አቅራቢያ ይገነባል ተብሎ የነበረው የ “ዋካንዳ” ፕሮጀክት ምን ላይ ደረሰ?

ምናባዊውን ዋካንዳ በአማራ ክልል ጭስ አባይ አካባቢ ዕውን ያደርጋል የተባለ ፕሮጀክት ሊገነባ እንደሆነ በመንግስት ሚድያዎች ጭምር በስፋት ተዘግቦ ነበር።

ይህ “ሀብ ሲቲ ላይቭ” በተባለ ድርጅት ይገነባል ተብሎ የነበረ የቴክኖሎጂ መንደር መሰረቱ የዛሬ ሁለት አመት ገደማ ለእይታ በቅቶ በነበረው “ብላክ ፓንተር” ፊልም ነበር።

የድርጅቱ ዋና ስራ አስኪያጅ ነኝ የሚሉት ሚካል ካሚል ዋልታ ቴሌቭዥን ላይ ቀርበው “እስከ 20 ቢልዮን ዶላር የሚፈጀው ፕሮጀክት ለ20 ሺህ ዜጎች የሥራ ዕድል ይፈጥራል፣ ኢትዮጵያንም በዓለም አቀፍ የቴክኖሎጂ ዘርፍ የተሻለ ደረጃም ያሰጣታል” ብለው ነበር። አክለውም ለመነሻ 3 ቢልዮን ዶላር ከአሜሪካ ባንኮች እንደተገኘ ተናግረው ነበር።

ፕሮጀክቱን እሰራለው ያለው ድርጅት ማን ነው?

ኢትዮጵያ ቼክ ማረጋገጥ እንደቻለው ፕሮጀክቱን በአማራ ክልል ባህርዳር ዙርያ ለማከናወን ያሰበው ሚካል ካሚል የተባለው ግለሰብ የመሰረተው ብሎክፕሌክስ የተባለው ድርጅት አሜሪካን ሀገር ውስጥ ከ2014 ጀምሮ ታግዷል።

ሚካል ካሚል ማናቸው?

በተለያዩ ድረ ገጾች ባደረግነው ፍለጋ ስለ ትምህርት ዝግጅታቸው፣ ስለ ሙያቸው፣ ስለ ስኬቶቻቸውም ይሁን የስራ አጋሮቻቸው ጥርት ያለ መረጃ ማግኘት አይቻልም። በ3 ቢሊዮን ዶላር ከአሜሪካ ወደ ኢትዮጵያ ተጉዞ በሳይንስ እና ቴክኖሎጂ የላቀ ከተማ ለመገንባት የቆረጠን ባለሙያ ፎርብስ እና ብሎምበርግ ሚድያዎች ሳያውቁት መቅረታቸው በራሱ ጥያቄ ያጭራል። ግለሰቡ ከሁለት አመት በፊት ከኤል ቲቪ ጋር ያደረጉትን ቃለ መጠይቅ ያጋሩበት የሊንክድኢን አድራሻቸው የካሊፎርኒያ ነዋሪ መሆናቸውን ይጠቁማል። ገጹ በእርግጥ የርሳቸው ከሆነ ሚካል ካሚል ብሎክፕሌክስ ኢንክ የተባለ ኩባንያ መስራች እና ስራ አስፈጻሚ ናቸው። ኸብ ሲቲ ኢንተርናሽናል ሆልዲንግስ የተባለውን ኩባንያም በባለቤትነት ይመራሉ። 21st-century “Strategist,” “Technologist,” “High-Tech Real Estate Developer,“ “Urban Technocrat and “Social Entrepreneur የሚሉ ተቀጥላዎችም አሏቸው። ብሎክፕሌክስ የተባለው ኩባንያ ከተመሰረተ አምስት አመታት ከአስር ወራት ተቆጥሯል የሚል መረጃ ብናገኝም ምን ሰሩ ለሚለው ምላሽ ማግኘት አይቻልም።

ሌሌች ፕሮጀክቶችን ሰርተዋል?

ዋካንዳን ይመስላል የተባለው መንደር ባለቤት ኸብ ሲቲ ላይቭ ተመሳሳይ ቅንጡ ከተማ በካሊፎርኒያ ኮምፕተን ለመገንባት ሐሳብ ነበረው። ዕቅዱ በተዓማኒ የመረጃ ምንጮች እና የዜና አውታሮች ትኩረት ባያገኝም እውቅና የሌላቸው ድረ ገጾች ስለ ጉዳዩ ጽፈዋል። በ2017 ለቀረበው ዕቅድ የተሰሩ ንድፎች አሁን በባሕር ዳር ይሰራል ለተባለው የተዘጋጁ መስለው ቀርበዋል። ዕቅዱ ግን እንደ ዋካንዳ ተምኔታዊ ብቻ ነበር። የኸብ ሲቲ ላይቭ ድረ ገጽም ቢሆን ይኸ ዕቅድ ተጨባጭ፣ አዋጪ እና የሚጨበጥ ለመሆኑ ማረጋገጫ አይሰጥም። በድረ ገጹ ላይ የሚገኘው የትዊተር መስፈንጠሪያ ከጉዳዩ ያለው ግንኙነት ወደ ማይታወቅ አድራሻ ይመራል። የፌስቡክ ገጻቸው ለመጨረሻ ጊዜ ስራ ላይ የነበረው 2017 ነበር። የኸብ ሲቲ ላይቭ ኢትዮጵያ የፌስቡክ ገጽ ደግሞ የባሰ ነው። ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ላይ እሰራለሁ ለሚል ግን ደግሞ ግልጽ በቂ መረጃ ለማይገኝለት ኩባንያ የአሜሪካ ባንኮች 3 ቢሊዮን ዶላር ይሰጣሉ? የአማራ ክልልም ይሁን የፌድራል መንግሥት ኩባንያውን ተቀብለው ሲያወድሱ ምን መተማመኛ አግኝተው ይሆን?

የኢትዮጵያ የመንግስት ስራ ሀላፊዎች ምን ይላሉ?

አብመድ በወቅቱ እንደዘገበው የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር የነበሩት ዶክተር ጌታሁን መኩሪያ “የአማራ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ የፕሮጀክቱ እውን መሆን ለክልሉ የቱሪዝም እንቅስቃሴ ወሳኝ በመሆኑ ተገቢውን ድጋፍ እንድናደርግ ደብዳቤ ፅፎልን እንጂ በኛ በኩል ስለ ፕሮጀክቱ የምናውቀው ነገር አልነበረም” ያሉ ሲሆን በሚገርም ሁኔታ አንዳንዶቹ በመንግስት ሀላፊዎች ተፃፉ የተባሉ ደብዳቤዎች የሀሰት እንደነበሩ አስነብቧል። በተፃፈለት የድጋፍ ደብዳቤ መሠረት ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በንድፈ ሀሳቡ ዙሪያ ከአጋር አካላት ጋር ውይይት ማድረጉንም አስታውሰው ውይይቱም ፕሮጀክቱ ለሀገሪቱ የቴክኖሎጂ ሽግግር በሚኖረው ፋይዳ ዙሪያ እንደነበር እና አሁን በምን ደረጃ ላይ እንዳለ እውቅና እንደሌላቸው ተናግረዋል፡፡

በሌላ በኩል በወቅቱ የአማራ ክልል ባህል እና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ የነበሩት ዶክተር ሂሩት ካሳሁን በበኩላቸው ስለ ደብዳቤው ምንም አይነት እውቅና እንደሌላቸው እና እርሳቸውም እንዳልፃፉት ተናግረዋል፡፡ የአማራ ክልል ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት ቢሮ ምክትል ኃላፊ ዶክተር ጌታሁን መኮንን በበኩላቸው በሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር አዳራሽ የፕሮጀክቱ ሀሳብ ቀርቦ ውይይት እንደተደረገበት እንጅ ጥናቱ ተጠናቅቆ የቀረበ እንዳልነበር ነው ያስረዱት፡፡ የቀረበውን ሀሳብ መሠረት በማድረግም ቢሮው ሙሉ ጥናቱ መቅረብ እንዳለበት “ሀብ ሲቲ ላይቭ” ለተባለው ድርጅት ሀሳብ አቅርቦ ነበር፤ ነገር ግን ድርጅቱ እስካሁን ጥናቱን አጠናቅቆ አለማቅረቡን ተናግረዋል፡፡

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::