ለኦሎምፒክ ወደ ጃፓን ያመራው የኢትዮጵያ ልዑክ በትናንትናው እለት በቶክዮ አየር ማረፊያ ሲደርስ ያጋጠመው ምንድን ነው?

ለቶክዮ 2020 ኦሎምፒክ ቀደም ብሎ፣ ማለትም ማክሰኞ ዕለት፣ ወደ ስፍራው ያቀናው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን እና የኦሎምፒክ ኮሚቴ ልዑክ እንዲሁም የዋና፣ ሳይክል እና ቴክዋንዶ ውድድር ተሳታፊዎች በትናንትናው እለት ቶክዮ በሚገኘው አየር ማረፊያ ሲደርሱ መጉላላት እንደደረሰባቸው ኢትዮጵያ ቼክ ከፌዴሬሽኑ ፕሬዝደንት ኮ/ር ደራርቱ ቱሉ አረጋግጧል። 

ኮ/ር ደራርቱ ለኢትዮጵያ ቼክ በሰጠችው ማብራርያ የልኡክ ቡድኑ አመራሮች ለስምንት ሰአት ገደማ አየር ማረፊያ ውስጥ የቆዩ ሲሆን ተወዳዳሪዎቹ ደግሞ ከዛም የበዛ ሰአታትን ቆይተው ዛሬ ጠዋት ወደ ሆቴላቸው ደርሰዋል። 

“ይህ የሆነው አብረውን ጉዞ አድርገው የነበሩ የሌላ አፍሪካ ሀገራት ሰዎች በኮቪድ ስለተጠረጠሩ ነበር፣ ፎርም መሙላቱ እና ሌሎች ሂደቶች ረጅም ግዜ ወስደዋል፣ የተቀናጀ ነገር አልነበረም” ብላ ኮ/ር ደራርቱ ስለሁኔታው አብራርታለች። 

የአትሌቲክስ ቡድኑ ገና ወደስፍራው ጉዞውን ያላደረገ ሲሆን በመጪው ቀናት ወደ ስፍራው ይጓዛል ተብሎ ይጠበቃል። 

ፎቶ: ኮ/ር ደራርቱ ቱሉ እና የአትሌቲክስ ቡድኑ መሪ የሆኑት ዶ/ር በዛብህ ወልዴ ወደ ቶክዮ ለመጓዝ ቦሌ አየር ማረፊያ በተገኙበት ወቅት የተወሰደ (via EAF)

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::